“ዕጣ ደርሷችኋል” በሚል ሰዎችን ያጭበረበሩ መያዙን ፖሊስ ገለጸ! 800 ጥይቶችም ተይዘዋል 

“ዕጣ ደርሷችኋል” በሚል ሰዎችን ያጭበረበሩ መያዙን ፖሊስ ገለጸ! 800 ጥይቶችም ተይዘዋል 

ኢትዮጵያ ነገ ዜናበዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተፈላጊ በሆነው በኮካ ኮላ ድርጅት ስም “ዕጣ ደርሷችኋል፤ አሸንፈዋል” በሚል የማጭበርበር ስራ እየተሰራ መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ አስታወቀ፡፡

“ኮካ ኮላ ለምርጥ ደንበኞቹ የሽልማት ፕሮግራም አዘጋጅቶ የነበረና ከተመረጡ ደንበኞች አንዱ የሆኑት እርስዎም የ200 ሺህ ዶላር ተሸላሚ በመሆንዎ እንኳን ደስ አለዎት” በሚል ማጭበርበሩ እንደሚከናወን የገለፀው ፖሊስ፣ ይህንንም ተከትሎም ለተለያዩ ጉዳዮች ማስፈፀሚያ የሚሆን 640 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ቶሎ ይላኩ እየተባሉ ዜጎች መጭበርበራቸውን አመልክቷል፡፡

“በተለያየ ጊዜና በተለያየ አካውንት 640 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ለአጭበርባሪዎቹ ገቢ ካደረጉ በኋላ የአጭበርባሪዎቹ ደብዛ ሲጠፋባቸው ተበዳዮች ለኮሚሽኑ መናገራቸውን የጠቀሰው ፖሊስ፣ ለአብነትም አንዲት ግለሰብ 92 ሺህ ብር በአጭበርባሪዎቹ አካውንት ላይ አስገብተው እንደተሰወሩባቸው፣ ሌላ አንድ አባት ደግሞ ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ 640 ሺህ ብር በተለያየ ጊዜና በተለያየ አካውንት ላይ ገቢ ካደረጉ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ ደብዛቸው መጥፋቱንና በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ አንድ መምህር 48 ሺህ ብር በአጭበርባሪዎቹ አካውንት ካስገቡ በኋላ ጉዳዩ ማጭበርበር እንደሆነ ተረድተው በድጋሚ ላኩ የተባሉትን ተጨማሪ ብር ሳይልኩ ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን ገልጿል፡፡

“ይህንን የወንጀል ተግባር ለመቆጣጠርና ለማክሸፍ ፖሊስ ባደረገው ጥረት አጭበርባሪዎቹ የባንክ አካውንትና ሲም ካርድ የሚያወጡት በሀሰተኛ /Forged/ መታወቂያ እንዲሁም የሚደውሉበት የስልክ መስመርም ጁንታው ቡድን ከዚህ በፊት ለእኩይ ተግባር ባሰራጫቸው ሲም ካርዶች ጭምር መሆኑም ታውቋል” ያለው ፖሊስ፣ በመሆኑም ዜጎች መሰል የማጭበርበር ድርጊት ሲያጋጥማቸው ብሩን ገቢ ከማድረግ አስቀድመው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመነጋገር እና ለፀጥታ አካላት በመጠቆም ህገ-ወጦችን ለህግ አስከባሪ አካላት አሳልፈው መስጠት እንደሚኖርባቸው አሳስቧል።

በሌላ በኩል፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከ800 በላይ ጥይቶችን በበቆሎ ውስጥ ደብቆ ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

ግለሰቡ የተያዘው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶቡስ ተራ ትንሿ መናኸሪያ ግቢ መሆኑንና ግለሰቡ በሁለት ከረጢት በያዘው በቆሎ ውስጥ 200 የብሬን እና 668 የክላሽንኮቭ በአጠቃላይ 868 ጥይቶችን ቀላቅሎ በመደበቅ በተሽከርካሪ ጭኖ ለማዘዋወር ሲንቀሳቀስ በወቅቱ በስራ ላይ በነበሩ የመናኸሪያው የስነ-ስርዓት ተቆጣጣሪዎች ጥርጣሬ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

LEAVE A REPLY