“እጅግ ፈታኝ በሆነ ህይወት ውስጥ የቆየው” የጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ አዲስ መጽሐፍ ተመረቀ!

“እጅግ ፈታኝ በሆነ ህይወት ውስጥ የቆየው” የጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ አዲስ መጽሐፍ ተመረቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከጤናው ጋር በተያያዘ ለአመታት እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ የህይወት መንገድ ውስጥ የቆየው የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ “ታልከል” የተሰኘ አዲስ መፅሐፉን ዛሬ አስመርቋል።

ላለፉት ረጅም ዓመታት የነፃ ፕሬስ ውጤቶች በነበሩት “ፈንዲሻ፣ ብሌን፣ ታሪክ፣ ወቅት፣ ዘጋቢ፣ ትኩሳት፣ ሞገድ፣ መሰናዘሪያ፣ ዋስትና፣ ምኒልክ፣ አስኳል፣ ሳተናው አና ኢትዮ ቻናል” በተሰኙ ጋዜጦች እንዲሁም “ዜጋ፣ ዕድሜ፣ ዋስትና እና ሮያል” መፅሔቶች በሪፖርተርነትና ዋና አዘጋጅነት ሲሰራ የቆየው ጋዜጠኛ አባተ ማንደፍሮ ያሳለፈውን ፈታኝ ህይወትና አዲሱን መፅሐፉን በሚመለከት ባስተላለፈው መልዕክት “የአለፈውን አንድ ዓመት በሕመም ምክንያት በቤት እና በሆስፒታልል ነው የአሳለፍኩት። ግን በእዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የዳንኩኝ ሲመስለኝና ጤንነት ሲሰማኝ ከቤት ገባ ወጣ አልኩኝ። ሥራም ጀመርኩኝ። በእዚህ መሃል ነበር “ታልከል” የተሰኘ መፅሐፌን ማተሚያ ቤት የሰጠሁት። ሃሳቤ እና ዕቅዴ ብዙ የነበረ ቢሆንም ጥር 17 ቀን 2013 መፅሐፌን በተረከብኩኝ ማግስት ሕመሙ አገርሽቶብኝ ዳግም ለሆስፒታል በቃሁ።

ከእዚህ ጊዜ ጀምሮ መፅሐፌን እንዴት አስመርቃለሁ፣ እንዴትስ ለአንባቢያን አደርሳለሁ? ስል ሳስብ እና ጤናዬን በተመለከተ የተሻለ ቀን ይመጣል እያልኩኝ ነበር የምጠብቀው ። በመሃል ግን “የምዕራፍ ፕሮሞሽን” ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ቢኒ ምዕራፍ እና “የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ማኅበር” በጋራ በአደረጉት እንቅስቃሴ መፅሐፌ ዛሬ ሚያዚያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት በጊዮን ሆቴል በአዲሱ ግሮቭ ጋርደን ዎክ ይመረቃል” ብሏል።

የምርቃት ዝግጁቱን ላሰናዱለት፣ ለዝግጅቱ ስኬት ድጋፍ ላደረጉለት፣ በአጠቃላይም “በህመሜ ጊዜ በተለያየ መንገድ ከጎኔ በመሆን የዛሬን ቀን እንዳይ አድርጋችሁኛል” ላላቸው ወገኖችም ምስጋናውን አቅርቧል።

LEAVE A REPLY