ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ ከ10ዐ ሺህ በላይ ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ በመሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ መርሐ ግብር የሙከራ ተግባር በ5 ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈረመ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአምስት ክፍለ ከተሞች፣ ከተለያዩ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴሎች፣ አጋዥ ድርጅቶች እና ባለሀብቶች ጋር በመተባበር ለጎዳና ተዳዳሪዎች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች የዕለት ጉርስ የሚሆን ምግብ ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ከባለ ኮኮብ ሆቴሎች እና አጋር ድርጅቶች ጋር ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን፣ በሙከራ ደረጃ የምገባ ማዕከል ለማደራጀት የሚያስችለውን ስምምነት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተፈራርመዋል።
“መርሃ ግብሩ ከትላልቅ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና ሱፐር ማርኬቶች የሚገኘውን ምግብ በመውሰድና በየማዕከሉ በማሰራጨት በቀን አንድ ጊዜ ለጎዳና ተዳዳሪዎች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች በማቅረብ ተጠቃሚ የሚያርግ ነው” ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የማህበር ቤት ምዝገባ ለተጨማሪ 10 ቀናት መራዘሙን አስታውቆ፣ ከመጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት ሲካሄድ በቆየው የማህበር ቤት ምዝገባ ከ8 ሺህ 500 በላይ የማህበር ቤት ፈላጊዎች መመዝገባቸውን አመልክቷል፡፡
ቀድሞ በተያዘው ዕቅድ መሰረት የምዝገባ ጊዜው ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ከህብረተሰቡ ተደጋግሞ በቀረበ ጥያቄ ምክንያት በመነሳት ለተጨማሪ 10 ቀናት መራዘሙንም ቢሮው አስታውቋል፡፡ ተመዝጋቢዎች ወደ ቢሮ መምጣት ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ /Online/ በቢሮው አድራሻ www.aahdab.gov.et አማካኝነት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ መመዝገብ የሚችሉ መሆኑም ተገልጿል።