ምርጫ ቦርድ ስላጋጠሙት ችግሮች ሪፖርት አቀረበ! ከስርአት የወጡ ቅስቀሳዎች መታየታቸው ተነገረ!

ምርጫ ቦርድ ስላጋጠሙት ችግሮች ሪፖርት አቀረበ! ከስርአት የወጡ ቅስቀሳዎች መታየታቸው ተነገረ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባና አጠቃላይ የኦፕሬሽን ሂደቶችን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ብዙኃን መገናኛ በተገኙበት ምክክር አካሄደ። በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችንም ሪፖርት አቅርቧል።

መድረኩን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የመሩት ሲሆን፣ ምርጫ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የሚያሣትፍ መድረክ እንደሆነና ከባለድርሻ አካላቱ መካከልም ፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ እንደመሆናቸው መጠን ስሕተቱንም ስኬቱንም እንዲያውቁ በማድረግ እየተራረሙ ለመሄድ በተከታታይ እየተዘጋጁ ያሉት መድረኮችን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

ዋና ሰብሳቢዋ በሰጡት ምላሽ፣ የመራጮች ምዝገባ በተፈለገው መልኩ እየሄደ ነው ማለት እንደማይቻል ገልጸው፣ ጉዳዩ በመራጮች ማስተማር ዙሪያ የተሠማሩ የሲቪል ማኅበራትና ፖለቲካ ፓርቲዎችም እገዛ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ከቁሳቁስ ሥርጭት አንጻር የሎጄስቲክስ ችግሮች እና አቅም፣ የአካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታና የጂኦግራፊ አቀማመጥ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን እስካሁን የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው አፋር እና ሶማሌ ክልሎች እንዳሉ፤ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባቀረቡት እሥርና ተያያዥ አቤቱታዎች ጋር በተገናኘ ፓርቲዎቹ በጥቅል እንዲህ ገጠመን ማለት ብቻ ሣይሆን በበቂ በማስረጃ አስደግፈው ቢያቀርቡ ተባብሮ መፍትሔ ለማሰጠት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሚቀጥለው ተከታይ ውይይት የመራጮች ምዝገባ ቀናትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ውይይት እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት እና ምዝገባን አስመልክቶ የሚቀጥሉት 7 ቀናት የሚኖረውን ሁኔታ ቦርዱ በተጨማሪ እንደሚያሳውቅ ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በሌላ በኩል፣ በስድስተኛው አገር አቀፍና አካባቢያዊ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ስሜት ቀስቃሽና ግጭትን ከሚያጋግሉ የቅስቀሳ ስልቶች ሊታቀቡ እና አገርን ከለየለት ትርምስ የመታደግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ኃይለማርያም ተመስገን እንደተናገሩት፣ አንዳንድ ፓርቲዎች ተፎካካሪዎቻቸውን ለመብለጥ ሲሉ ብቻ ሕዝብ እና ሕዝብን ሊያጋጩ የሚችሉ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ የቅሰቀሳ ስልቶችን ይከተላሉ፡፡

ይህም አገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር አኳያ ወደለየለት ትርምስ ውስጥ ሊከታት የሚችል በመሆኑ ፓርቲዎቹ ከጊዜያዊ ጥቅማቸው ባለፈ የአገር ህልውና ቀጣይነትን ታሳቢ አድርገው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

LEAVE A REPLY