የትኛውም ምድራዊ ምክንያት ዝምታውን ተገቢ ሊያደርገው የሚችል አይደለም። ኢትዮጵያ ትረጋጋ ዘንድ ማዕከላዊ መንግስቱ ጠንካራ እንዲሆንና በሁለት እግሩ እንዲቆም በግሌ ማበረታታትን፣ ሞራልና ድጋፍ መስጠትን እንደ ትክክለኛ አካሄድ ወስጄው ቆይቻለሁ። አሁንም ይህ አካሄድ ስህተት ነው ብዬ አላምንም።
የለውጥ መንግስት በመሆኑ እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ችግሮችን እንደ ለውጥ ጊዜ ክስተቶች በመውሰድ መንግስትን ረጅም ርቀት በትዕግስት መመልከት እንዳለብን አምኜበት ዘልቄአለሁ። ህወሓት ያበላሸውን ለማስተካከል፣ ያቆሸሸውን ለማጽዳት፣ ያጣመመውን ለማቃናት ጊዜ እንደሚፈልግና የሞት ሽረት ትግል እንደሚጠይቅ በመረዳት የመንግስትን ጉድፎችና ክፍተቶች የለውጥ ዘመን ባህሪያት በሚል እልህንና ቁጭትን ዋጥ ማድረጉን በመምረጥ ሰብቼአለሁ።
ኢትዮጵያ ምርጫ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ቅርቃር ውስጥ ናት። ህወሓት ከአደጋ ጋር አላትሟት፣ አሁንም በዚያው የአደጋ ሽክርክሪት ናላዋን አዙሮ ሊደፋት የመጨረሻውን እድሉን እየሞከረ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ከምግዜውም በላይ የህልውና አደጋ ተጋርጦባት እንዳለች በግሌ እረዳለሁ። የመንግስት ደካማነትን እያወኩም ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ አሁን ያለውን መንግስት እግር ሰብሮ የሚጥል ትግል ኢትዮጵያን ለበለጠ አደጋ ምናልባትም በማግስቱ ኢትዮጵያ ስለምትባል ሀገር ማውራት የማንችልበት፣ ሀገር አልባ የምንሆንበት ምዕራፍ የሚጀመርበት ስለመሆኑ ጥርጣሬ የለኝም።
ነገር ግን ይህን መንግስት መደገፍ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ጭፍጨፋዎችን፣ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን መደገፍ ወይም ተገቢነት አለው የሚል ድምዳሜ መስጠት ማለት አይደለም። በእርግጥ የውሽማ ለቅሶ ሆኖ አውጥተን የማናለቅስበት ምክንያቱ ነገን በመፍራት ነው። ይሄ መንግስት ቢወድቅ የሚፈጠረው አደጋ አሁን ከምናየው፣ ከምንሰማው በላይ የሆነ፣ እንደ ሀገር መቆም የማንችልበት ሁኔት መከተሉ የማይቀር ነው። አንዳንድ ጊዜ የበለጠውን ቀውስ ለማስቀረት ባለው መጥፎ ሁኔታ ውስጥ በትዕግስት መቆየት የሚያዋጣና የተሻለ ነገር ግን አስቀያሚ ምርጫ ሊቀርብልን ይችላል። አሁን በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን አድርጌ አስበዋለሁ።
ይህም ቢሆን ግን በሰሞኑ ዓይነት ክስተት ውስጥ የመንግስት ዝምታ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ ምን እንዳይመጣ ነው የምንፈራው የሚል ጥያቄን የሚጭር ነው። ትዕግስቱ በዝቷል። ዝምታው ለከት አጥቷል። የትኛውም ምክንያት የሰሞኑንም ሆነ ወለጋ ላይ የተከሰተውን እንድናምን የሚያደርገን አይደለም። አጣዬ ስትነድ፡ ካራቆሬ ስትጨስ፡ ሸዋሮቤት ነዋሪ አልባ ስትሆን፡ በመቶ ኪሎሜትሮች ርቀት የመንግስት ባለስልጣናት ቅንጡ ዘመናዊ ህንጻ እያስመረቁ ሲምነሸነሹ ማየት ደም የሚያፈላ ነገር ነው። ራስ ሳይጠና ጉተና እንዲሉ የሀገሪቱን የውስጥ ደህንነት መጠበቅ ሳይችል መሀል ሀገር ሲታመስ አይቶ እንዳላየ በዝምታ ለተቀመጠ የደህንነት መስሪያ ቤት እንዲህ ያለ ቸበርቻቻ አስፈላጊ መሆኑ ፈጽሞ አልታየኝም።
ቢያንስ ስለጉዳዩ ማብራሪያ መስጠትና ዜጎችን ማረጋጋት አንድ ነገር ነው። ዝምታው ምንድን ነው? በመንግስት የታቀደ፡ ሆን ተብሎ እየተፈጸመ ያለ ነው በሚል በስፋት እየተነገር ያለው የህዝብ ስሜት ትክክል ነውን? በእርግጥም ይህ ዘመናዊ ህንጻዎች የተገነቡለትና በፈንጠዚያ የተመረቁለት የደህንነት መስሪያ ቤት እያለ ነው መሀል ሀገር ሰው የሚረግፈው? እውነት ለመናገር በተደበላለቁ ስሜቶች ውስጤ እየተናጠ ነው። ተስፋ የጣልኩበት የለውጡ መንግስት ምቾት በሚነሱ አካሄዶቹ ትዕግስቴን በሀይለኛው እየተፈታተነኝ ነው። ሀገር ለማዳን ቁርጠኝነት አላቸው የምላቸው አመራሮች ምን እየጠበቁ ነው? ቢያንስ ዝምታቸውን ለመስበር እንደምን ወኔ አጠራቸው? ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ምን እንዳትሆን ብለው ነው እየጠበቁ ያሉት? ሸዋሮቢት ህዝብ እያለቀ፡ ወለጋ ላይ ህጻናት እየታረዱ፡ አዲስ አበባ ላይ መምነሽነሽ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?
ጉዳዩን አውጥቼ አወረድኩት። ምክንያት ካለ ብዬም ተመራመርኩት። ሀገር ለማዳን ነው ብለው ከሆነም ብዬ የሚመለከታቸውን አንዳንድ አመራሮች አነጋገርኩ። የምርጫ ወቅት ስለሆነ ምርጫውን ለማደናቀፍ እንደሆን ብዬም በዚያ ዙሪያ የባለሙያዎችን አስተያየቶች አዳመጥኩ። ግብጽ እጇ እንዳለበትስ? ብዬም ጠየኩ።
ምንም የሚያሳምን ምክንያት አላገኘሁም። የትኛውም ሰበብ ምክንያት ከአንጀት ጠብ የሚል መልስ ሊሆን አይችልም። ሰው ነው የሚሞተው። ሀገር ነው እየፈረሰ ያለው። መንግስት አከባቢ ጉዳዩን ውጭያዊ ለማድረግ የተለያዩ ሰበቦችን ደረደሩልኝ እንጂ አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጡኝ አልቻሉም። ግራ የሚያጋባ ነገር ነው።
አሁንም መንግስት ይውረድ የሚል ጀብደኝነት ውስጥ መግባት አልፈልግም። ምን ተይዞ ነው ከዚያ አደገኛ አቋም ላይ የሚደረሰው? ነገር ግን መንግስት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጫናውን በየአቅጣጫው መጨመር እንዳለብን ተሰምቶኛል። መንግስት ባይወርድ እንኳን እንዲፈርድ በምንችለው ሁሉ ግፊት ማድረግ የጊዜው መሰረታዊ ተግባር መሆን ይኖርበታል። መፈንጠዙና መምነሽነሹ በቁስል ላይ እንጨት የመጨመር ያህል የሚያም በመሆኑ መንግስት ለጊዜው ከቸብርቻቻው ቆጠብ ብሎ የሰውን ሞት እንዲያስቆም፡ ሀገሪቱን ማዳን የቅድሚያ ተግባሩ አድርጎ እንዲሰራ ጊዜ የማይሰጠው እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ይኖርብናል። እውነት ለመናገር ሁኔታው ከአእምሮ በላይ ነው። ይበቃል። የህዝባችን ስቃይ ከገደፉ አልፏል። ይህ ሁሉ ሆኖ፡ ህዝብ አልቆ የሚመጣ ብልጽግና በአፍንጫችን ቢወጣ እመርጣለሁ።
መንግስት ሆይ ፍረድ! የምር መንግስት ሁን! ህዝብህን አድን!