ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወቅታዊ የአገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ “ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግስታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን” በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል።
ከትናንት ምሽት ጀምሮም “አብን ከምርጫው ራሱን አገለለ” የሚል ዜና በተለያዩ ሚዲያዎች ሲሰራጭ መዋሉ ተስተውሏል። ይሁንና ጉዳዩን በማስመልከት ባደረግነው ማጣራት እየተሰራጨ ያለው ዜና ሀሰተኛ መሆኑንና ፓርቲው በዚህ ጉዳይ ላይ የያዘው ምንም አይነት የተለየ አቋም እንደሌለ አረጋግጠናል።
አብን በትናንት መግለጫው፣ በአሁኑ ሠአት በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለው አሰቃቂ ጭፍጨፋና ማፈናቀል እንዲሁም አጠቃላይ የሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልፆ “ህዝቡ ራሱን ከጥቃት የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን ሊጠቀምና ተደራጅቶ ለራሱ ደህንነት ዘብ እንዲቆም” በማሳሰብም ትግሉንም ከፊት ሆኖ እንደሚመራው አስታውቋል።
ይሁን እንጂ አብን ምንም እንኳ ሀገሪቱ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል መደላድል አለመኖሩን የገመገመ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር በተያያዘ ያሳለፈው አንዳችም ውሳኔ አለመኖሩን ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ለማረጋገጥ ችለናል።