– ኮማንድ ፖስቱ ስራ ጀመረ!
– “የተኩስ ልውውጥ ቢቆምም ጥቃት ፈፃሚዎቹ አሁንም በከተማዋ መሽገዋል”
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሰሜን ሸዋ ዞን ስር የምትገኘው እና የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ዋና መቀመጫ የሆነችው የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ታጣቂዎች ቀድመው ጥቃት የጀመሩባት ስፍራ ስትሆን፣ በታጣቂዎች በተፈጸመባት ጥቃት ሙሉ በሙሉ መውደሟ እየተነገረ ነው።
ጥቃት በተፈፀመባቸው ቦታዎች ህፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶች መገደላቸው እንዲሁም ከጥቃት ለማምለጥ መንቀሳቀስ የማይችሉ አቅመ ደካሞች ጭምር በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተቃጥለው መሞታቸው ተሰምቷል።
በአጣዬ የተጀመረው ጥቃት ወደ ካራቆሬ፣ ማጀቴ፣ መኳይ፣ ሸዋሮቢት እና ሌሎች በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ወዳሉ ቀበሌዎች ተስፋፍቶ መቆየቱን ያመለከቱ ምንጮች “ይሁንና ከፍተኛ ጉዳት ባስተናገደችው አጣዬ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በታጣቂዎቹ ጥቃት ወድመዋል” ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻዲቅም አጣዬ ከተማ “ሙሉ ለሙሉ በታጣቂዎቹ ጥቃት መውደሟን” አረጋግጠው “በአብዛኛው ከተቃጠለችው እና ከወደመችው አጣየ ከተማ የሸሹ ዜጎች በደብረብርሃን፣ መሀል ሜዳ፣ በርግቢ፣ ይምሎ፣ መሀልሜዳ በሚባሉና የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ተጠልለዋል። ከአጣየ ከተማ ብቻ ከ10 – 15 ሺህ የሚገመቱ ዜጎች ተፈናቅለዋል። በአጣየ በርካታ የግለሰብ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ የመንግስት ተቋማት ፈርሰዋል፣ ውሃና መብራት የለም። እስረኞች ተለቀዋል። የከተማው አመራሮችም ከነዋሪዎች ጋር ከተማውን ጥለው ሸሽተዋል” በማለት የደረሰውን ውድመት ተናግረዋል።
ዛሬ የሸዋሮቢት ከተማ አንጻራዊ መረጋጋት እንደሚታይባትና ከጥቃቱ ለማምለጥ ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ናቸውም ታውቋል።
በተያያዘ፣ ከትናንት ምሽት ጀምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተሞቹ በመግባት ላይ መሆኑና በዚህ ጥቃት የሞቱ፣ የቆሰሉ፣ የተፈናቀሉ ሰዎችን እና የወደሙ ንብረቶችን መጠን የሚያጣራ ቡድን ጥቃቱ ወደ ተፈጸመባቸው ቦታዎች መንቀሳቀሱ የተገለፀ ሲሆን፣ የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተውና በአገር መከላከያ ስር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስትም “የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ስራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራውን” ዛሬ መጀመሩ ተነግሯል።
ኮማንድ ፖስቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ፣ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪ/ሜ ውስጥ የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን፣
እንዲሁም መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግስት ተቋማትን፣ የግለሰብ መኖርያ ቤትን እና ማንኛውነም ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጥልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ መከልከሉን አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋና አካባቢው ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ዛሬ መለስተኛ መሻሻሎች እንደታዩበት፣ የተኩስ ድምጽ መቆሙን፣ ነገር ግን አጥፊው ሃይል በአካባቢው መሽጎ እንደሚገኝ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገልፀዋል፡፡
በአጣዬና አካባቢው ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝና የጠላትን ሃይልን ከአካባቢው ለማጽዳት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ግዛቸው ሙሉነህ “ከአካባቢው አሁንም የጠላት ሃይል አልጸዳም፣ መሽጎ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የጠላትን ሃይል ማጽዳት ያስፈልጋል። በለዋል።
በማያያዝም የክልሉ ህዝብ በተለይ ወጣቶች ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝና ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ትብብር ማድረግና በስጋት ያሉትም በየአካባቢያቸው ተደራጅተው ራሳቸውን እንዲከላከሉ፣ ወደ አካባቢያቸው የጠላት ሃይል ሲመጣ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
የሰሞኑን ጥቃትና ውጥረት በሚመለከት አስተያየት ከሰጡ ምሁራን መካከል ገዢው ፓርቲ ብልፅግናን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ አንዱ ሲሆኑ፣ ሁኔታውን በማስመልከት “አማራ እያለቀ ነው፣ አብይ አህመድ ግን የመስሪያ ቤት አጥር ሳይቀር እያስመረቀ ይውላል። በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀውና ተፈናቅለው፣ በመጠለያ እጦትና ምግብ አቅርቦት እየተቸገሩ ባሉበት ሁኔታ እነሱ የመስሪያ ቤታችን አጥር ምን ይምሰል፣ ግቢያችንስ እንዴት ይዋብ እና የሰራተኞቻችን የደንብ ልብስ ምን አይነት ይሁን በሚለው ሀሳብ ይጨነቃሉ። ከዚህም አልፈው አንዳንዶቹ ደግሰውም አጥር ያስመርቃሉ። ሁኔታዎቹ የሁለት አለም ሰዎች ያሰኘናል። ይባስ ብሎ ዋናው መሪያችን በሰላም ጊዜ የሚከወን ተግባርን በማድነቅ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ” ብለዋል።
በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፅና ቀጥተኛ ሃሳባቸውን በመሰንዘር የሚታወቁት የታሪክ ተመራማሪው አቻምየለህ ታምሩ በበኩላቸው “ይህ አሸባሪ ኃይል ይዟቸው የሚታዩት አብዛኛዎቹ መሳርያዎች በትንሹ ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚሸጡ ናቸው። ደግሞ እንዲሁ የሚገኙ አይደለም። ሌላው ቀርቶ የመከላከያ ሰራዊቱ እንኳን ከበርካታ ክላሽ ያዥ ጋር ነው በመሃል ጣል እያደረገ በአብዛኛው የሚጠቀምባቸው። የክልል መንግስታት መሳርያ አጥተው በኮንትሮባንድ የሚገዙበት ጊዜ ሁሉ እንዳለ ይነገራል። ያውም አያገኙምኮ። ይህኛው በየትም በየትም ተብሎ ይደርሰዋል። ገራሚ ነው መቸም። ተአምር! ይህኛው ኃይል ግን ክላሽ ምን ያደርግልኛል ብሎ መትረየስና ስናይፐር ነው የታጠቀው። በማለት ትዝብታቸውን አጋርተዋል።