ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል እና ለተለያዩ አካዳሚክ ክፍሎች የተገነባውና በጸሀፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ታሪኩ የተሰየመው የጥናትና ምርምር ማዕከል ካምፓስ) ዛሬ በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ።
የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ጋር በመሆን መርቀው ስራ ያስጀመሩት ይህ ማዕከል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማረ ዜጋ ከማፍራት ጎን ለጎን በጥናት እና ምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።
በዚሁ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባዋ “ዩኒቨርስቲው በጸሀፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ካምፓስ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች እና ባህልን በማዳበር ለትውልድ ለማስተላለፍም ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወ/ሃና በበኩላቸው “የጸሀፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ታሪኩ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ማዕከል በ75 ሚሊየን ብር ወጪ የመማሪያ፣ የተማሪዎች ማደሪያ፣ ዘመናዊ ላይብረሪ እና ልዩ ልዩ የምርምር ክፍሎችን ያካተተ ነው” ሲሉ ተናገረዋል።
በመርሐግብሩ ማጠቃለያ በዩኒቨርስቲው ለረጅም ጊዜ ላገለገሉ፣ በጥናት እና ምርምር ሰራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ፕሮፌሰሮች እና የጸሀፌ ትዕዛዝ ወልደመስቀል ታሪኩ ቤተሰቦች የእውቅና እና የምስጋና ሽልማት መሰጠቱን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡