ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ “ሱዳንና ግብፅ የሚያሰሙትን የጦርነት ነጋሪት” በርዕሰ አንቀፁ አወገዘ!

ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ “ሱዳንና ግብፅ የሚያሰሙትን የጦርነት ነጋሪት” በርዕሰ አንቀፁ አወገዘ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ዘ ስታንዳርድ የተሰኘው ዝነኛ ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ባስነበበው ዘገባ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚያሰሙትን የጦርነት ነጋሪት ኮንኗል፡፡ የጦርነት ነጋሪት ከማሰማት ይልቅ ጉዳዩን በውይይትና በድርድር እንዲፈታ ማድረግ እንዳለባቸውም መክሯል።

የአዘጋጆቹን አቋም በሚያንፀባርቀው ርዕሰ አንቀጹ “ሀገራቱ የአባይ ወንዝ የ11 የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሀብት መሆኑን ሊዘነጉ አይገባም” ያለው ዘ ስታንዳርድ፣ በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ ሱዳንና ግብጽ የደረሱበት የውኃ ክፍፍል ስምምነት የተፋሰሱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ስለሚጥስ ኢትዮጵያ ስትቃወመው እንደነበር አስታውሷል።

ሁሉም የወንዙ ተጋሪ ሀገራት ውኃውን በኀላፊነት መንፈስ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረስ እንዳለበት ያተተው ጋዜጣው፣ ግብጽና ሱዳን ወንዙ የእነርሱ ብቻ እንደሆነ አድርገው የሚያራምዱትን አቋም ማስተካከልና በተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ አለመረጋጋት ለመፍጠር ከመስራት መቆጠብ እንዳለባቸውም መክሯል።

በኮንጎ/ኪንሻሳ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ባለመስማማት መጠናቀቁን ተከትሎ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ “አንዲት ጠብታ ውኃ ብትነካ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ወደ አለመረጋጋት ይገባል” ማለታቸውን ያስታወሰው ዘ ስታንዳርድ፣ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው የኤሌክትሪክ ኀይል በማመመንጨት ለመጠቀምና ለጎረቤት ሀገራትም ለማካፈል መሆኑን ጠቅሶ፣ ሀገራቱ ከመራራቅ ይልቅ ተቀራርበው አለመግባባቱን በመነጋገር መፍታት እንደሚገባቸውና የኪንሻሳው ድርድር አለመሳካት የሁሉ ነገር መጨረሻ ባለመሆኑ ተከታታይ ንግግሮች ሊደረጉ እንደሚገባ አመልክቷል።

LEAVE A REPLY