“መንግስት ጥቃቶችን ለማስቆም አልቻለም፤ ራሱም የችግሩ አካል ሆኖ ተገኝቷል” በሚል ሲወገዝ ዋለ!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከሰሞኑ በአጣዬ እና አካባቢው ከተሞች በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የተፈፀመውን ዘርን መሰረት ያደረገ ዘግናኝ ጭፍጨፋና ከባድ የንብረት ውድመት እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች (በጉራፈርዳ፣ በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከልና ሌሎች አካባቢዎች) በአማራነታቸው ምክንያት በዜጎች ላይ ሲፈፀም የቆየውን ግድያ፣ ጥቃትና ማፈናቀል የሚያወግዙ የተቃውሞ ድምፆች በአማራ ክልል ከተሞች ሲያስተጋቡ ውለዋል።
ከትናንት በስቲያና ትናንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በደሴና ደብረ ማርቆስ ከተሞች የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬም በወልዲያ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ባሕር ዳር፣ ሐይቅና ሰቆጣ ከተሞች የቀጠለ ሲሆን፣ በሁሉም ከተሞች “መንግስት የዘር ጥቃቶችን ለማስቆም ኃላፊነቱን ባለመወጣቱና የችግሩ አካል ሆኖ በመገኘቱ” ሲወገዝ ውሏል።
“አስከሬን እየቆጠሩ የንፁሃንን ሞት ማስላት ይብቃ! አማራን መግደልና ማፈናቀል ይቁም! አማራ አይሰበርም! እኛ የአባቶቻችን ልጆች አማራዎች ነን! አማራን ማሳደድ ይቁም! ህፃናትን መግደልና ከተማ ማፍረስ ጀግንነት አይደለም! አማራ በማንነቱ ሊጠቃ አይገባም!” የሚሉና ሌሎች በርካታ የተቃውሞ መፈክሮች በተስተጋቡባቸው የዛሬ ሰልፎች በሚሊዮኖች የሚገመቱ የክልሉ ተወላጆች አደባባይ ወጥተው ብሶትና አቋማቸውን አሰምተዋል።
በዋናነት በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሱትን ግድያ እና ጥቃቶች የሚያወግዙ ድምጾች በተሰሙባቸው በነዚህ ሰልፎች “በአማራ ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ ጭፍጨፋዎችን ማስቆም የነበረበት መንግስት ኃላፊነቱን አልተወጣም” በሚል ከመወገዙም ባሻገር “በተለያዩ አካባቢዎች በተፈፀሙ ግድያና ጥቃቶች ውስጥ እጁ አለበት፤ የችግሩ አካል ሆኖም ተገኝቷል” የሚሉ አቋሞች ተንፀባርቀዋል።
ሰልፉን በማስመልከት ያነጋገርናቸው በርካታ የሰልፉ ተሳታፊዎች “ከእንግዲህ በኋላ ሁሉም ነገር ሊያበቃና ሊቆም ይገባዋል” የሚል ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ለመረዳት ሲቻል፣ አንድ አስተያየት ሰጪም “የአማራ ሕዝብ፣ መንግስት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ያስጠብቅ ብሎ ብዙ ጊዜ ጠይቋል።
ወገኖቻችን በማንነታቸው አይፈናቀሉ ብሎ ወትውቷል። የቀጠለው ግን የባሰ ሆነ። በቡድን መሳርያ የታገዘ ሽብር ተፈፀመበት። ከተሞች ወደሙ። ህፃናትና አዛውንቶች ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ በእሳት ተቃጠሉ። ጥቃቱ ባልታጠቁት ላይ ብቻ አልነበረም። የንፁሃንን ሕይወት ለመታደግ የተሰለፉ የአማራ ፀጥታ ኃይሎች በደባ እንዲጠቁ ተደርጓል።
ጥቃቱ የአማራን ፀጥታ ኃይል ማዳከምንም አላማው ያደረገ ነው። አማራ የሚተማመንበት ልዩ ኃይሉን ነው በሚል ድምዳሜ ተጠንቶ የተፈፀመ ነው። አሁን አደባባይ የወጣው ሕዝብ በርካታ ስሜቶችን ችሎ ቆይቷል። በየቀኑ አማራ እየተገደለ ችሏል። የታጠቀ ኃይል እያጠቃው ችሏል። ያን ሁሉ የመበደል፣ ያን ሁሉ የመከዳት ስሜት ችሎ የከረመ ሕዝብ ነው አሁን አደባባይ የወጣው” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማስመልከት “ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግስታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን” ሲል የአቋም መግለጫ ያወጣውና ትግሉን ከፊት ሆኖ እንደሚመራ ያሳወቀው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባስተላለፈው አዲስ መልዕክት “የአማራ ሕዝብ በገንዛ አገሩ ውስጥ እንደጠላት ተቆጥሮ የተከፈተበትን የተደራጀና የተቀናጀ መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በማያወላዳ መልኩ የመቀልበስ እንቅስቃሴ በይፋ ጀምሯል።
ይህ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ እንዲጀመር የፌዴራሉም ይሁን የክልሉ መንግስት በሕዝባችን ላይ ሳያባራ ለሦስት አመት የቀጠለው የጅምላና የተናጥል ግድያ እንዲሁም ጅምላ ማፈናቀልን ለማስቆም ምንም አይነት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ከመረጋገጡም በላይ በእርግጥም ችግሩ መንግስታዊ ዘመቻና ስምሪት የሚሰጥበት መሆኑ በተጨባጭ የታወቀ ኃቅ በመሆኑ ጭምር ነው። እናም የተጀመረው ሕዝባዊ ሰላማዊ ትግል የግዴታ ዘላቂ እልባት በማምጣት መቋጨት ይኖርበታል” በማለት አስታውቋል።
“በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ባልተቋረጠ መልኩ የሚፈፀሙት መንግስት መራሽ የዘር ፍጅቶች በገለልተኛ ኮሚሽን በጥልቀት ተጣርተው በቀጥታ በጥቃት ውስጥ የተሳተፉ፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ መንግስታዊ መዋቅርን ለጥቃት ማስፈፀሚያነት ያዋሉ፣ ያስተባበሩና የተመሳጠሩት አካላት ማንነት ለሕዝብ በይፋ እንዲገለፅና ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ አጠቃላይ ተጎጅዎችን በተመለከተ ተጣርቶ ዝርዝር ሪፖርት ይፋ እንዲደረግ” ሲል ያመለከተው አብን፣ ከሰልፎቹ ዋና ዋና አላማዎች አንዱ “በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ሕዝብ ላይ ያንዣበቡ ዘር ተኮር ጥቃቶች ፍፁም የማይደገሙ ስለመሆናቸው የማያወላዳ ማረጋገጫ እና የደኅንነት ዋስትና በይፋ እንዲሰጥ ማስቻል” መሆኑንም ገልጿል።