|| አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ||
ሚያዚያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መበቶች ጉባኤ፡- ኢሰመጉ ከዚህ ቀደም በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ይፋ በማውጣት መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ሲወተውት የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተለይም በቅርብ ጊዜ ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መግለጫውን ባዘጋጀበት ወቅት ባወቀው ልክ አሳውቆ ጥሰቶቹ ከመባባሳቸው በፊት መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ ካልሆነ ተጠያቂነት የማይቀር መሆኑን ገልፆ ማሳሳቡ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን በአገራችን ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰና እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ሰብአዊ መብቶች ምንም ዋስትና
የላቸውም ማለት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
በዚህም በአጣዬ ከተማና አካባቢው ስለተፈፀመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ኢሰመጉ ከዚህ ቀደም ባወጣው ልዩ መግለጫ እንዲሁም በቅርቡ መጋቢት 25/2013ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ማድረጉና ምክረ- ኃሳቦችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሰለባዎች ከጉዳታቸው ሳያገግሙ እንዲሁም አካባቢው የፀጥታ ስጋት እንዳለበት ታውቆ አስፈላጊው ጥንቃቄ መወሰድ ሲገባው ከሚያዚያ 6/2013ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 አካባቢ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በተፈፀመው በከባድ መሳሪያ የታገዘና ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሰዎችን ለሕልፈት፣ ለንብረት ውድመት እንዲሁም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡
ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በአጣዬ ዙሩያ ባሉት ማለትም በማጀቴ፣ በቆሪ ሜዳ፣ በዙጢ፣ በዩሎ ቆላ፣ በሙሉ በርጊቢ፣ ካራ ቆሬ፣ ኔጌሶ፣ ኩሪቱሪ እና በሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁና ከባድ መሳሪያ በታጠቁ ኃይሎች ተኩስ ተከፍቶ በማጀቴ በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን፣ በካራ ቆሬ የፀጥታ ኃይሎች መቁሰላቸውን፣ ነዋሪዎች አካባቢዎቹን ለቀው ወደሌላ የገጠር ቀበሌዎች መሰደዳቸውንና ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን እንዲሁም አጣዬ፣ ቆሪሜዳ፣ ዙጢ፣ ካራቆሬ የተባሉ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ እንደወደሙ ኢሰመጉ ከአካባቢው የሰበሰበው መረጃ ያመላክታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሸዋ ሮቢት ከተማ ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ ከሚያዘያ 07/2013ዓ.ም ጀምሮ ለተሸከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት በማቆሙ ሰዎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ ይገኛል፡፡
ከዚህም ሌላ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች እንደሚገደሉ፣ የገበሬ ቤቶችና የእህል ጎተራ እንደሚቃጠል እንዲሁም ሰዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ኢሰመጉ በየጊዜው ከሚሰራቸው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ለመረዳት ችሏል፡፡
በተጨማሪም በትግራይ ክልል ነዋሪው አሁንም ለችግር መጋለጡንና አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው እንዲሁም ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሁንም ያልተሻሻለና እንደልብ ለመንቀሳቀስ ምቹ እንዳልሆነ ከቦታው ለኢሰመጉ የቀረቡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተመሳሳይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ሰዎች በሕገወጥ ታጣቂዎች እንደሚገደሉ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን በጉማይዴና አማሮ ልዩ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች፣ እንደሚገሉ፣ የአካል ጉዳት እንደሚደርስባቸው እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ እንደሚታሰሩ ለኢሰመጉ አቤቱታዎች ቀርበዋል፡፡
በተመሳሳይ በአፋር ክልል በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው ግድያና የንብረት ውድመትም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የደረሰበትን አስከፊ ደረጃ ማሳያ ነው፡፡
በዚህም ኢሰመጉ ከላይ የተጠቀሱትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አስመልክቶ ምርመራ እያደረገ የሚገኝና ግኝቱን ይፋ የሚያደርግ መሆኑን እያሳወቀ እስከዛው ግን ድርጊቶቹ በምንም መስፈርት ተቀባይነት እንደሌላቸውና የሚወገዙ መሆኑን ለመግለፅ ይወዳል፡፡
በዚህም አገራችን በተለያዩ አቅጣጫዎች ሰዎች የሚሞቱባት፣ አካል የሚጎድልባት፣ የሚፈናቀሉባት እና ንብረት የሚወድምባት፤ በአጠቃላይ ሰብአዊ መብቶች ዋስትና ያጡባት አገር ሆናለች፡፡ የድርጊቶች አፈፃፀምም ሆነ አዝማሚያው አገራችን ላይ የተደቀነውን ትልቅ ችግር አመላካች በመሆኑ የአገራችን ቀጣይ እጣ ፋንታ ኢሰመጉን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡
ስለሆነም መንግስት ድርጊቱን መከላከልና ማስቆም ስላልቻለበት ምክንያት እንዲሁም ስለቀጣይ
እርምጃዎቹ ይፋዊ ማብራሪያ እንዲሰጥ ኢሰመጉ ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ሰዎች ኃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በሚገልፁበት ጊዜ እስር፣ ወከባ እንዲሁም መሰል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይፈፀምባቸው መንግስት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ያሳስባል፡፡