የአማራ ክልል ከተሞች የተጀመረው ተቃውሞ ሰልፍ ለ3ኛ ቀን ዛሬም ቀጥሏል!

የአማራ ክልል ከተሞች የተጀመረው ተቃውሞ ሰልፍ ለ3ኛ ቀን ዛሬም ቀጥሏል!

“አማራ ክልልን በመክበብና በመወጠር ሀገር ለመበተን የሚንቀሳቀስ ኃይል አለ” የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች “በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ፣ ማሳደድ፣ ጥቃትና ማፈናቀል ይቁም” በሚል ከትናንት በስቲያ የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬም ለ3ኛ ቀን መቀጠሉ ታውቋል።

ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ካስተናገዱ የአማራ ክልል ከተሞች መካከል ደብረብርሃን ከተማና ላሊበላ ከተማ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የየከተሞቹ ነዋሪዎችም ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ባለፉት ሁለት ቀናትና ዛሬም በቀጠሉት የተቃውሞ ሰልፎቹ ዘርን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃቶች፣ የንብረት ውድመትና ማፈናቀሎች እንዲቆሙ ተጠይቋል፤ መንግስትም በብርቱ ተወቅሷል።

የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች በዛሬ የተቃውሞ ሰልፋቸው እንደሌሎች ከተሞች ሁሉ ተመሳሳይ ጥያቄና አቋሞችን ከማንፀባረቃቸው ባሻገር፣ በቅርቡ ከፖለቲካው ዓለም በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ያገለሉት አቶ ልደቱ አያሌው ወደውጭ አገር ሄደው እንዳይታከሙ መከልከላቸውንም ሲቃወሙ እንደዋሉም ከስፍራው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች እየተካሄዱ የሚገኙትን ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች በሚመለከት መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ” ለረዥም ጊዜ ሲሰራ የቆየው አማራን የማዳከም ስትራቴጂ መሬት የነካ መሆኑን ጠላቶቻችን በተደጋጋሚ እየነገሩን ይገኛሉ።

በአሁኑ ሰዓት አማራ ክልልን በሁሉም አቅጣጫ በመክበብና በመወጠር ሀገር የመበተን ግቡን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ኃይል አለ” በማለት መናገራቸው ተመልክቷል።

ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ትናንት ማምሻውን በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ ከተሞች የቀጠሉት ሰልፎች ዓላማ በተለያየ ጊዜና ቦታ የአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲቆም መንግሥትን የሚጠይቅ፣ በተለይም ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየና አካባቢው በጽንፈኛው የኦነግ ሸኔ ኃይል የተከፈለውን የህይወት መስዋእትነትና የደረሰውን ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ለማውገዝ መሆኑን ገልፀው፤ በሰልፉ ላይ የተገኘው ህዝብም ተቃውሞና ሀዘኑን በምሬት መግለፁን ተናግረዋል።

ሰልፉ በየከተሞቹ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ በመሆኑ ለአስተባባሪዎችና ለተሳታፊው ህዝብ ያላቸውን አክብሮትና ምስጋና የገለፁት አቶ ግዛቸው “የአማራ ህዝቦች ችግር በሰልፍ ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን በመረዳት ወጣቱና መላው ህዝብ ለዘለቄታዊ መፍትሔዎች ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

ከዚሁ በማያያዝም “የኢትዮጵያም ሆነ የአማራ ህዝብ ጠላቶች ለረዥም ዓመታት መጠነ ሰፊ ሴራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩበት ሁኔታ ግዘፍ ነስቶ በገቢር የተገለጸበት ዘመን በመሆኑ ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመተባበር እንዲሁም ሰከን ብሎ በመምከር ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ በደም ፍላት መፍታት አንችልም።

ከተባበርን የማንወጣው መከራ፣ የማንሻገረው ምንም አይነት ችግር የለም። በመሆኑም የትኛውም የፖለቲካ ኃይሎች ይሁኑ መላው ህዝባችን የአማራን ህዝብ ውስጣዊ አንድነት በማጠናከር የአማራን ህዝብ ሞት እና አንግልት ለማስቆም በሰከነ መንገድ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY