የመራጮች ምዝገባ ቀን ሊራዘም መሆኑ ተጠቆመ!

የመራጮች ምዝገባ ቀን ሊራዘም መሆኑ ተጠቆመ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ለ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ “ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ መሆን” መደረግ በሚገባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመምከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ከምርጫ ቦርድ የስራ ኃላፊዎችና ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የመራጮች ምዝገባ እንደሚራዘም ጠቁመዋል።

የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ የመራጮች ምዝገባ ቀን እንደሚራዘም በጠቆሙበት በዚሁ ንግግራቸው ተጨማሪው ቀን ምን ያክል እንደሚሆን በግልፅ ባያሳውቁም ቦርዱ ተወያይቶ የሚወስን እና የሚያሳውቅ መሆኑን ግን ተናግረዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከውይይቱ በኋላ “የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሂደት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሠራን ነው። ባለፈው ከክልል አመራሮች እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባካሄድነው ስብሰባ፣ ቀሪ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ እና ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ማስቀመጣችን ይታወሳል። ዛሬ ቀጣይ ስብሰባ አካሂደን፣ ክንውኑን ገምግመናል። ሲሉ በፌስቡክ ገፃቸው አስታወቀዋል።

አያይዘውም ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ ልዩነቶች በጥይት ሳይሆን በምርጫ ካርድ አማካኝነት የሚፈቱበት ነው። በምርጫ ሂደት፣ ዜጎች የተማመኑበትን በሙሉ ልብ ለመምረጥ እና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ለመገንባት ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ዕድል ያገኛሉ። መጪው ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያስፈነጥር እንደ መሆኑ፣ በጋራ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ያስፈልገናል። ነገን እንዲወስኑ፣ ዛሬ ይመዝገቡ!”  በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY