“170 የጁንታውና 53 የሸኔ አባላትን ጨምሮ” በአዲስ አበባ አደገኛ ወንጀለኞች መያዛቸውን ፖሊስ...

“170 የጁንታውና 53 የሸኔ አባላትን ጨምሮ” በአዲስ አበባ አደገኛ ወንጀለኞች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ኦፕሬሽን፣ በተደራጀ አኳኋን አቅደው ከባድ የዘረፋና የግድያ ወንጀል ፈፅመዋል ያላቸውን 70 ወንጀለኞች እንዲሁም በዘረፋ ወንጀል ላይ የተገኙ 34 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገለፀ።

ለዚሁ የወንጀል ተግባር መፈፀሚያ ሊውሉ የነበሩ 4 ቦንብ፣ 23 ሽጉጦች፣ 4 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 3,580 የሽጉጥ፣ 200 የብሬን እና 3171 የክላሽንኮቭ ጠመንጃ በድምሩ 6,951 ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ሊያውል መቻሉን አስታውቋል፡፡

ፌደራል ፖሊስ በመግለጫው፣ ወንጀለኞቹ ለዚሁ እኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ ይጠቀሙበት የነበረ 906,040 የኢትዮጵያ ብር እና 8,382 የአሜሪካን ዶላር በቁጥጥር ስር መዋሉንም ገልጿል።

በተመሳሳይ “ጁንታው በፈፀመው ጥቃት የተሳተፉና በተለያዩ መንገዶች አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በወንጀል ተግባር መሳተፋቸው በህዝብ ጥቆማ የተደረሰባቸው 170 ተጠርጣሪዎችና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው 53 የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ በፌዴራል ፖሊስና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች በጥምረት በመጣራት ላይ ይገኛል” ያለው ኮሚሽኑ፣ የከተማዋ ነዋሪ የፀጥታ ኃይሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርጋቸው ኦፕሬሽኖች እንደወትሮው ከፖሊስ ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

 

LEAVE A REPLY