የአማራ ክልል የተቃውሞ ሰልፍ አድማሱን አስፍቶ ዛሬም ለ4ኛ ቀን እንደቀጠለ ነው!

የአማራ ክልል የተቃውሞ ሰልፍ አድማሱን አስፍቶ ዛሬም ለ4ኛ ቀን እንደቀጠለ ነው!

-ዛሬ በባህር ዳር ባንኮች ላይ ጥቃት መፈፀሙ ተወገዘ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ሰሞኑን በአጣዬና አካባቢው፣ ቀደም ብሎም በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ/መተከል፣ በደቡብ ጉራ ፈርዳና ሌሎች አካባቢዎች የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶችን መነሻ አድርገው “የአማራ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ይቁም” በሚል የተጀመሩት የተቃውሞ ሰልፎች ከቀን ወደ ቀን አድማሱን እያሰፋ ዛሬም ለአራተኛ ቀን በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች መቀጠሉ ታውቋል።

ዛሬ በጎንደር፣ መርዓዊ፣ መርሳ፣ አዴት፣ እንጅባራ፣ ኮምቦልቻ፣ ሞጣ፣ ደብረታቦርና ቆቦ እንዲሁም በደብረብርሃን ለሁለተኛ ቀን የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፣ የየከተሞቹ በርካታ ነዋሪዎችም አደባባይ ወጥተው የተቃውሞ ድምፃቸውን ሲያሰሙ መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በተጠቀሱት የአማራ ክልል ከተሞች ዛሬ የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ላለፉት ሶስት ቀናት በክልሉ ከተደረጉት ሰልፎች ጋር ተመሳሳይ አቋምና ስሜት የተንፀባረቀባቸው መሆኑን ለመረዳት ሲቻል፣ በሁሉም ሰልፎች “አማራነት ላይ አነጣጥረው የሚፈፀሙት ግድያዎች፣ ማሳደዶች፣ ማፈናቀሎችና የንብረት ውድመቶች በአስቸኳይ ይቁሙ። አጥፊዎችም ለፍርድ ይቅረቡ” የሚሉ ተቃውሞና ጥያቄዎች መንፀባረቃቸውን ከየአካባቢዎቹ የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።

እንደ መረጃዎቹ ከሆነ “መንግስት የዜጎቹን በሰላም የመኖር ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን አልተወጣም” በሚል መንግስትን የሚወቅሱና የሚያወግዙ የተለያዩ መልዕክቶች መተላለፋቸውን ለመረዳት ተችሏል።

በሌላ በኩል፣ ባለፉት ቀናት የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎችን ያስተናገደችው የአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር ዛሬ ቤት የመቀመጥ አድማ ውስጥ መሆኗና ዛሬ ከተማዋ እንቅስቃሴ አልባ ሆና ጎዳናዎቿም ጭር ብለው መዋላቸውን በስልክ ካነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፣ በከተማዋ ጥቂት ቦታዎችም ከተቃውሞው አላማዎች ውጪ የሆኑ ድርጊቶች መፈፀማቸው ተመልክቷል።

“በከተማ በሚገኙ ሶስት የኦሮሚያ ባንኮች ላይ ጥቃት በመክፈት የመስኮት መስታወቶችን የመሰባበር ድርጊት ተፈፅሟል። ይህም ሆነ ተብሎ የተቃውሞዎቹን ዓላማ ለማሳትና የእርስበርስ ግጭትን ለማስነሳት ታስቦበት የተደረገ የሰርጎ ገቦች ተግባር በመሆኑ በፅኑ እናወግዘዋለን” በማለት የገለፁልን የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የክልሉ ልዩ ኃይል አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ጭምር በወሰደው ፀጥታ የማስበከር ዕርምጃ ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ማረጋጋቱንም ነግረውናል።

በተያያዘ፣ ወቅታዊውን ሁኔታ አስመልክቶ የባህር ዳር አስተዳደር ባወጣጣው መግለጫ፣ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ በደረሰው ህይወት መጥፋት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ሃዘን እንደተሰማው ገልጾ “ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ ተወላጆችን ሰርተው ለመለወጥ በሚታትሩበት ወቅት በማንነታቸው እየለዩ መግደል አረመኔነት ነው” ሲል አውግዟል።

“የሰልፉ አላማ ሞት እና መፈናቀል ይቁም የሚል ነው” ያለው የአስተዳደሩ መግለጫ፣ ይሁንና “አንዳንድ ፅንፈኞችና የወቅቱን የክልሉን እና የአማራን ህዝብ ነባራዊ ሁኔታ ያልተረዱ ሰላማዊ ሰልፉን ለማበላሸት ሙከራ ሲያደርጉ ነበር” ብሏል።

“በሰልፉ ላይ የክልሉን እና የከተማውን ህዝብ የማይመጥኑ ንግግሮች፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን የሚያሸማቅቁ መፈክሮችና የክልሉን አመራሮች ስብዕና የሚነኩ መፈክሮች እና ንግግሮች፣ በፀጥታ አካላት ላይ የታየ ማንጓጠጥ እና ማመናጨቅ፣ አመራሩን ለመከፋፈል አንዱን በማኮሰስ ሌላውን በማጀገን የተደረገው ቅስቀሳ ፍፁም ስህተት ነው” ሲልም የሰልፉን ዓላማ አቅጣጫ የማሳት እንቅስቃሴዎች መስተዋላቸውን ገልጿል።

LEAVE A REPLY