ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄነራል ባጫ ደበሌ ዛሬ ለአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ሀሰተኛ የሌላ ክልል መታወቂያን በማውጣት ወደ ሱዳን ሊሸሹ በነበሩ የቀሩ ርዝራዥ የጁንታው ተላላኪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
“እነዚህ የጁንታው አባላት ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ የሌላ ክልል መታወቂያ በመያዝ ከሀገር ሊሸሹ ሲሉ ሰራዊቱ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቷል” ነው ያሉት ሌ/ጄነራል ባጫ።
የዚህ ድርጊት ዋነኛ አላማ አባላቱን ወደ ሱዳን በማሸሽ ከዚያ ሆኖ ሀገር ውስጥ ያሉትን ታጣቂ ሀይሎች በሽምቅ ውጊያ በማሰማራት ሀገር መበጥበጥ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ “እርምጃ በተወሰደባቸው በሁሉም የጁንታው አባላት እጅ ላይ ሀሰተኛ መታወቂያው ተገኝቷል” በማለትም ሌ/ጄነራል ባጫ ደበሌ በመግለጫቸው ተናግረዋል።