አሜሪካ “የትግራይን ቀውስ፣ የኢትዮ ሱዳን ግጭትና የህዳሴ ግድቡን የሚከታተል” ልዩ መልዕክተኛ ሾመች!

አሜሪካ “የትግራይን ቀውስ፣ የኢትዮ ሱዳን ግጭትና የህዳሴ ግድቡን የሚከታተል” ልዩ መልዕክተኛ ሾመች!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አሳሳቢ የሆኑትን ፖለቲካዊ፣ የደኅንነትና የሰብአዊ ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነትና ይህን ሁኔታ በቅርበት መከታተል እእንዲቻልም አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ሾሙ።

ባይደን በትላንት መግለጫቸው  “አሁን ላይ አሜሪካን የሚያሳስበው ነገር ቢኖር የትግራይን ግጭትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያለው ተለዋዋጭ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውጥረት እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ውዝግብ ነው” ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ፣ በኢትዮ ሱዳን ድንበር ያለውን ውጥረትና የበታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የገቡበትን አለመግባባት በቅርበት ለመከታተል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የፈጠሩትን ተልዕኮ እንዲፈፅሙ የተሾሙት አዲሱ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

በተያያዘ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት “ወቅታዊው የትግራይ ሁኔታ ያሳስበኛል” ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ምክር ቤቱ በተደጋጋሚ በትግራይ ጉዳይ ሲነጋገር ቢቆይም በአባላቱ መካከል ስምምነት ባለመደረሱ የጋራ አቋም ሳይዝ መቆየቱን የጠቀሰው መግለጫው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብና ለረጂዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን አድንቆ “ከችግሩ ስፋት አንፃር የሰብዓዊ እርዳታው ሊጠናከር ይገባል ብሏል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጠው ድጋፍ በተመሳሳይ ማደግ ይኖርበታል። በክልሉ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ወሲባዊ ጥቃት በአስቸኳይ መቆምና አጥፊዎችም ተለይተው በሕግ ሊጠየቁ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

ይሁንና፣ የፀጥታው ምክር ቤት መግለጫን ተከትሎ በመንግሥታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተልዕኮ በሰጠው ምላሽ “በትግራይ የሚካሄደው የሕግ ማስከበር ጉዳይ በሀገሪቱ ሕግ የሚመራና የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ነው” በማለት አሳስቦ፤ በትግራይ ተፈፀመ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ወሲባዊ ጥቃት እንደሚያጣራ ገልጿል።

LEAVE A REPLY