የአርቲስት መስፍን ጌታቸው ስንብት!

የአርቲስት መስፍን ጌታቸው ስንብት!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየዙምራ ፊልም፣ የሰው ለሰው እና የዘመን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች፣ እንዲሁም የቀን ቅኝትና መንታመንገድ የሬዲዮ ተከታታይ ድራማዎች ደራሲና ተዋናይ የነበረው አርቲስት መስፍን ጌታቸው፣ በኮቪድ 19 ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አርቲስቱ፣ ከቀናት በፊት የኮቪድ 19 ፅኑ ህሙማን ማዕከል ወደሆነው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ተወስዶ የህክምና እርዳታ ሲደረግለት የነበረ ሲሆን፣ በተደረገለት የህክምና ርብርብ ግን ከትናንት ማምሻ በላይ ህይወቱን ማቆየት አልተቻለም።

መስፍን ጌታቸው ከደራሲነቱና ተዋናይነቱ በተጓዳኝ ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ እንዲሁም በግዮንና ፍትሕ መፅሔቶች ስለአገሩ ጉዳይ ግድ የሚለውና ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑን የሚመሰክሩ በርካታ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ መጣጥፎችን ያቀርብ ነበር።

አብዛኛው ሰው በፍርሃት ቆፈን ውስጥ በነበረበትበህወሓት የአፈና ዘመንመስፍን ጌታቸው፣ በእስር ላይስለነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝና ሌሎች የነፃነት ፋኖዎች ደፍሮ የፃፈ እውነተኛ የጥበብ ሰው እንደነበርም ብዙሃን ይመሰክሩለታል።

በርካታ የሙያ ጓደኞቹና በቅርበት የሚያውቁት እንደሚሉት፣ መስፍን ጌታቸው እንደ ጅረት ፈስሶ የማያልቅና ምንጩ የማይደርቅ የፈጠራ ሀሳብ ባለቤት ነበር። የቀን ቅኝት የሬዲዮ ድራማ ለረጅም አመታት  በአዳዲስ ሞጋች፣ ጠያቂና አመራማሪ ጉዳዮች ተሞልቶ በየቀኑ ሲቀርብ የነበረው ሀሳብ የማይነጥፍበት ደራሲ መስፍን ጌታቸው የሚፅፈው ስለነበር ነው ሲሉ የጥበብ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ። 

በዙምራ፣ በሰው ለሰው እና ዘመን የቴሌቪዥን ድራማዎች ያሳየንም ይህንኑ የሀሳብ ሀብቱን ነበር።

ጠይሙ፣ ኮልታፋውናበገዛ ቁመቱ ማጠር ጭምር ቀልድ ፈጥሮ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ማዝናናትን ይችልበት እንደነበርየሚነገርለት መስፍን ጌታቸው፣ ከትንሹም ከትልቁም ተግባብቶ ማደር የሚችል የፍቅር ሰው እንደነበርም ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

በኢትዮጵያ ሬድዮ ዝነኛ የነበረው የቀን ቅኝት ድራማ ደራሲ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተላልፎ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የሰው ለሰው ተከታታይ ድራማ ደራሲ እና ተዋናይ የነበረውና ሌሎች በርካታ የጥበብ ስራዎችን በድርሰት፣ በአዘጋጅነት እና በትወና አስተዋፆኦ ያበረከተው ሁለገቡ ባለሞያ አርቲስት መስፍን ጌታቸው፣ ባለትዳር እና የሶስት ልጆች (የሁለት ሴት እና የወንድ ልጅ) አባት የነበረ ሲሆን፣ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በኮቪድ-19 ምክንያት በተወለደ 50 አመቱ ሚያዝያ 17 ቀን 2013 . ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

የቀብር ስነ ስርአቱም ዛሬ ሚያዝያ 18 ቀን 2013 . ከቀኑ 9:00 ሰአት በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቹ፣ በርካታ የሙያ ጓደኞቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት በክብር ተፈፅሟል።

የኢትዮጵያ ነገ ዝግጀት ከፍል ባልደረቦች የአገር ሀብትና ባውለታ በሆነው በአርቲስት መስፍን ጌታቸው ህልፈት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን፣ ፈጣሪ ነፍሱን እንዲምር እና ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን እንዲሰጥ እንመኛለን፡፡

LEAVE A REPLY