እኔ እምፈልገው || በእውቀቱ ስዩም

እኔ እምፈልገው || በእውቀቱ ስዩም

እውነት ለመናገር፥እኔ እምፈልገው
ካንቺ ጋር መጋባት
ይህን ሐምሌ ፊቴን፥ ደጋግሞ ማራባት
ከወፎች ጋር መንቃት፥ በጊዜ ቤት መግባት

“ምንም ድሀ ቢሆን፥ ባይኖረውም ሀብት
ከደጃፍ ሲቀመጥ ፥ደስ ይላል አባት”

ለሚል መናኛ ጥቅስ ፥ ኑሮየን ማይመጥን
ሲሻኝ በየባንኩ ፥ስፈልግ በሳጥን
የተረፈኝ ገንዘብ
ደጃፍ ላይ ቁጭ ብየ ፥ድሀ የምታዘብ

ተምሳሌትነቴ ፥ የሚዳረስ ባለም
ሞዴል አባዋራ፥ ተብየ ምሸለም
አገሬን ማስከበር
ህዝቤን ማስተባበር
የልጅ ልጅ አፍርቼ፥ በመቶ አመት ሙቼ
ስላሴ እምቀበር
ምኞቴ ይህ ነበር፥

እውነት ለመናገር ፥እኔ እምፈልገው
ወንደላጤ ኑሮ
በሴቶች መከበብ ልክ እንዳውራ ዶሮ
ጊዜ ጥሎኝ ቢሄድ ፥ ቀን ቢገሰግስም
መላው ጭንቅላቴ ፥ገብስማ ቢለብስም
ላቅማዳም ነው እንጂ ፥ለትዳር አልደርስም
ደሞ
ዘር መዝራት እርሜ ነው ደጋግሜ ባርስም
ባለመኖር ላሉት፥ስቃይ አላወርስም
ቢፈልግ ሌላው ህዝብ
ይፈልፍል እንደዝንብ
ይባዛ እንደ እንጉዳይ
አገር ስራው ያውጣው ፥ሰው የራሱ ጉዳይ
የራሴ ፈጣሪ፥ ነኝ የራሴ ገዳይ

እውነት ለመናገር
እኔ እምፈልገው
ምንድር ነው? ምንድነው?

ገንዘብ ቢመዘበር፥ በገንዘብ ይተካል
እድሜ ለጉልበትሽ፥ በላቡ ለሚያድር
በውርስ፥ በስጦታ፥ ግፋ ቢል በብድር ፤

በቆጠብነው ቁጥር
ጊዜ ነው የሚያጥር
እድሜ ነው የሚያልቀው
የምንፈልገውን፥ በቅጡ ሳናውቀው::

(አዳምኤል)

LEAVE A REPLY