ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከፌዴራልና ከክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ፖሊስ የተውጣጡ አባላትን የያዘ የምርመራ ቡድን፣ በአጣዬና አካባቢው እንዲሁም ከቅማንት ማንነት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን የወንጀል ድርጊት የሚያጣራ መርማሪ ቡድን ወደስፍራዎቹ መላካቸው ተገለፀ።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ገረመው ገብረጻዲቅ ዛሬ እንደገለፁት፣ በአጣዬና አካባቢው በሰው ህይወት መጥፋት፣ በአካል መጉደል፣ በንብረት መውደምና በሰዎች መፈናቀል የደረሰው ጥፋት ተራ ግጭት ሳይሆን ለዘመናት የተገነባ ከተማን ያወደመ አስከፊ የወንጀል ድርጊት በመሆኑ የወንጀል ድርጊቱን በልዩ ትኩረት ለማጣራት የፌዴራልና የክልሉ ተቋማት የጋራ የምርመራ ቡድን በማቋቋም፣ እቅድ በማውጣትና አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ስራ መገባቱ ተመልክቷል።
“በደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ሃብት ውድመት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የማቅረብ ስራ ይከናወናል። የምርመራ ቡድኑ ባጭር ጊዜ ውስጥ ስራውን ከማጠናቀቅ ባሻገር በማጣራት ሂደቱ የሚገኘውን ውጤት በተከታታይ ለህዝቡ የሚገልጽ ይሆናል” በማለት ያመለከቱት ዐቃቤ ሕጉ፣ የታክቲክና የቴክኒክ ስልቶችን ተጠቅሞ በሚከናወነው ምርመራ የየአካባቢው ማህበረሰብ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ ማስረጃ በማቅረብና ምስክር በመሆን እንዲተባበር ጠይቀዋል።
በአጣዬና ዙሪያ ወረዳዎች ከተፈፀመው ጥቃትና ከደረሰው ውድመት በተጨማሪ በማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋ አካባቢ ከቅማንት ማንነት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን የወንጀል ድርጊት የሚያጣራ መርማሪ ቡድንም ወደ ስፍራው መላኩን የተናገሩት ዐቃቤ ሕግ አቶ ገረመው ገብረጻዲቅ፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የህዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልፀው “በክልሉ በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ማስቆም የሚቻለው በየደረጃው የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሲቻል መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።