የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር መሾሙ ተሰማ!

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር መሾሙ ተሰማ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ላለፉት ሁለት አመታት በኃላፊነቱ ሲሰሩ የቆዩት አበረ አዳሙ ከቦታው መነሳታቸው ከተሰማ ከቀናት በኋላ፣ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ ኮሚሽነር መሾሙ ተገለጸ።

ከሁለት ሳምንት በፊት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና በተፈፀሙ ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ፣ በተደረገው ሹም ሽር ከሚያዚያ 19/2013 ዓ.ም ጀምሮ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው በኃላፊነት እንዲሰሩ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ መመደባቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከትናንት ጀምሮ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን እንዲመሩ የተሾሙት ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፣ ከ3 ዓመት በፊት በፌደራል ፖሊስ ውስጥ በኃላፊነት ከመመደባቸው አስቀድሞ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።

ከዚህ በፊትም በደቡብ ወሎ ዞን የኮምቦልቻ ከተማ ፖሊስ አዛዥ፣ የአምባሰል ወረዳ ፖሊስ አዛዥ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ተመልክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ዋና ኮሚሽነር ሆነው ያገለገሉት ኮሚሽነር ተኮላ፣ በሠላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውና በፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲሁም የፋይናንስ እና ሎጂስቲክስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ሆነው ማገልገላቸውና በሠላም እና ደኅንነት የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው ተነግሯል።

በአጣዬና በዙሪያው በሚገኙ የሰሜን ሸዋ ዞን በርካታ ወረዳዎች ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት እስካሁን ቁጥሩ በትክክል የማይታወቅ የሰው ሕይወት ማለፉና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ከቀያቸው መፈናቀላቸው አሁን ለተደረገው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሹም ሽር ዋናው ምክንያት መሆኑ ይነገራል።

LEAVE A REPLY