2 ሺህ 705 ታራሚዎች “ይቅርታ” ተደረገላቸው!
ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅና በክልሉ የተፈጠሩ ግጭቶችን በማረጋጋትና የክልሉን ሕዝብ የመኖር ዋስትና ለማስከበር ያለመታከት እየሠራ ነው” አሉ።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን፣ በልዩ ኃይሉ መካከል “መከፋፈል አለ” ተብሎ የሚናፈሰው አሉባልታ ፍጹም ሐሰት መሆኑንና ልዩ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አንድነት የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እየሠራ እንደሆነ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል፣ የክልሉ ይቅርታ ቦርድ በወሰነው መሰረት በአማራ ክልል በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ 2 ሺህ 705 ታራሚዎች “ይቅርታ” መደረጉንና ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ከዛሬ ጀምሮ መውጣት መጀመራቸውን የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለምሸት ምሕረቴ ተናግረዋል፡፡
“በተለያዩ ወንጀሎች እስራት ተፈርዶባቸው አንድ ሦስተኛ የእስራት ጊዜያቸውን የጨረሱ እና በማረሚያ ቤት የሥነ ምግባር ለውጥ ማሳየታቸው የተረጋገጠላቸው ታራሚዎች ናቸው በይቅርታ እንዲለቀቁ የተወሰነው።
ሕጻን ይዘው የታሰሩ ሴቶችና ነብሰ ጡር እስረኞች ከሆኑ ደግሞ ከተፈረደባቸው የእስራት ጊዜ አንድ አምስተኛውን ካጠናቀቁ የይቅርታው ተጠቃሚ ይሆናሉ” ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው “ይሁን እንጂ ይቅርታው ከ15 ዓመት በታች የሆነች ልጃገረድ አስገድዶ የደፈረ፣ ፍጻሜ ባገኘ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ፍጻሜ ባገኘ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዲሁም በሙስና ወንጀል 10 ዓመትና ከዚያ በላይ እስራት የተፈረደባቸው ታራሚዎችን አያካትትም” ብለዋል።