ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አቶ ልደቱ አያሌው ከአገር እንዳይወጡ፣ በፌደራል ፖሊስ እና በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች ጥያቄ ፍርድ ቤት አፅንቶት የቆየውን የእግድ ውሳኔ የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሽሮታል።
በአቶ ልደቱ ላይ ተላልፎ የቆየው የእግድ ውሳኔ፣ የግለሰቡን በህይወት የመኖር መብት የሚጥስ እንደሆነ የጠቀሰው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ እግዱን በዋነኛነት ውድቅ ያደረገባቸውን ምክንያቶች ጠቀሷል።
ፖሊስ በደብዳቤው የጠቀሳቸው አቶ ልደቱ ተከስውባቸው በነበሩባቸው ሁለት የወንጀል ጉዳዮች ነጻ መባላቸውንና አቶ ልደቱ በአቤቱታቸው ላይ የጠቀሱትን የልብ ህመም በሁለተኛ ምክንያትነት መውሰዱን ከዚሁም ጋር ተያይዞ አቤት ባዩ ወደ አሜሪካ ሀገር ሄደው ባይታከሙ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር መመልከቱን አመልክቷል።
“ፖሊስ በአቶ ልደቱ ላይ ያወጣው የጉዞ እግድ የግለሰቡን እንደ ልብ የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብት የሚገድብ ነው” ያለው ፍርድ ቤቱ፣ በእነዚህ ዋነኛ ምክንያቶች የጉዞ እግዱ እንዲሻር መወሰኑንም አስታውቋል።