ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በትንሳኤ በዓል ዕለት፣ በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 03 ልዩ ስሙ ሸመንተሪያ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በከተማዋ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ የ9 ሰዎች ህይወት የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ባንታለም ግርማ ተናግረዋል።
ከጠዋቱ ሁለት ሰአት ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ሰዓታት ዝናብ ሲጥል መቆየቱን፣ በዚህም ሳቢያ ርዝመቱ 50 ሜትር የሆነ የግንብ አጥር በሶስት ቤቶች ላይ ተደርምሶ ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ሞት ማስከተሉን ምክትል ኢንስፔክተሩ አስረድተዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ የሶስት ወር ጨቅላ ህፃን ልጅን ጨምሮ የአምስት አመትና የሁለት አመት ታዳጊዎች እንደሚገኙበት እና ከሟቾቹም ሶስቱ ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል።
“በስፍራው ተጨማሪ አደጋ እንዳይደርስ ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ነው” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊው “ሰሞኑን ከብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ በተሰጠው ትንበያ መሰረት በቀጣይ ቀናትም ከባድ ዝናብ እንደሚጥል ስለሚጠበቅ ህብረተሰቡ ለእንደዚህ አይነት አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁኔታዎችን በተቻለ መጠን እንዲከላከል” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።