የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዶ/ር ሙሉ ነጋ ተነስተው ዶ/ር አብርሃም በላይ መሾማቸው ተገለፀ!

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዶ/ር ሙሉ ነጋ ተነስተው ዶ/ር አብርሃም በላይ መሾማቸው ተገለፀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ኃላፊ ሆነው ላለፉት 6 ወራት ክልሉን ሲመሩ የነበሩት ዶ/ር ሙሉ ነጋ ከኃላፊነታቸው ተነስተው፣ ዶ/ር አብርሃም በላይ በዋና ኃላፊነት እንዲሰሩ መሾማቸው ተገለፀ።

ዶክተር አብርሃም በላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው መሾማቸውን የገለፁት የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሃፍታይ ገ/እግዚአብሔር፣ ዶ/ር ሙሉ ለምን ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ ያሉት ነገር የለም።

አዲሱ ተሿሚ ዶ/ር አብርሃም በላይ ቀደም ሲል የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሲያገለግሉ የቆዩና የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ የካበተ የስራ ልምድ እንዳላቸውም ይነገራል።

ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ የኢፌዲሪ የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን እስከ ሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ ደረጃ የደረሱ፣ ከ1996–1998 ዓ.ም በመከላከያ ኢንጂነሪግ ኮሌጅ በአስተማሪነት ያገለገሉ፣ ከ1998 ዓ.ም ኢመደኤ (የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ) ሲቋቋም ከተመረጡት ሙያተኞች አንዱ በመሆን እስከ 2010 ዓ.ም በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎችና የተቋሙ ም/ዋ ዳይሬክተር ሆነው
የሰሩ ናቸው።

ከ2007 – 2009 ዓ.ም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራ የሃገር አቀፍ የምርምር ካውንስል ቴክኒካል አማካሪ አባል የነበሩ ሲሆን በ2008 ዓ.ም በሃገር ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተዘጋጀ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤት ውድድር በመወዳደር አሸናፊ ሆነው የ3.9 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ ለመሆን የቻሉ፣ ከ2010-2011 ዓ.ም በሳይበር ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ቦርድ ሰብሳቢነት ያገለገሉ፣ ከቋሚ ስራቸው ጎን ለጎን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመዘዋወር የሚያስተምሩ እነደነበር ተመልክቷል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የንግድ ባንክ ቦርድ አባል በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ እንዲሁም ከ2010 ዓ.ም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር እስከሆኑበት ድረስ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን ከሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመቀናጀት በዘርፉ እጅግ የላቁ ተግባራትን ያከናወኑ መሆናቸውም ተነግሯል።

በተያያዘ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ኃላፊ ሆነው ላለፉት 6 ወራት ክልሉን ሲመሩ የነበሩት
ዶክተር ሙሉ ነጋ ከሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምሕርት ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።

LEAVE A REPLY