ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- በድንገተኛ ህመም ህይወታቸው እንዳለፈ የተገለፀው የቀድሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ አስክሬን በአዲስ አበባ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ወደ ባህርዳር ተመልሶ ስርዓተ ቀብራቸውም በባህር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን መፈፀሙ ታውቋል።
የኮሚሽነር አበረ አዳሙ አስክሬን ከባህርዳር አየር ማረፊያ ጀምሮ እስከ መኖሪያ ቤታቸውና ስርዓተ ቀብራቸው ድረስ ከፍተኛ የክብር አቀባበልና አሸኛኘት እንደተደረገለት ታወቋል።
በስፍራውም፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አዲሱ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩና በርካታ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች መገኘታቸውን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።