ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሰየሙት ልዩ መልዕክተኛው ጄፍሪ ፊልትማን፣ የትግራይን ጦርነት ጨምሮ በሕዳሴው ግድብ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብ ዙሪያ መፍትሄ የማፈላለግ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው፣ ለ9 ቀናት የሚቆይ
ጉዟቸውን የጀመሩት ባለፈው ሰኞ ሚያዚያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።
በትግራይ ቀውስ እና በሌሎች ክፍለ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ከሱዳን፣ ከግብፅ፣ ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር፣ ሴናተሮችን ያካተተ የልዑካን ቡድናቸውን አስከትለው ጉዞ የጀመሩት ልዩ መልዕክተኛው ፊልትማን፣ በትግራዩ ቀውስ ዙሪያ ግጭት ቆሞ ሰላማዊ መፍትሄ ለማስገኘት እስከ ድርድር የሚደርስ ሀሳብ እንዳላቸው በስፋት ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከአፍሪቃ ህብረትና ከመንግስታቱ ድርጅት ሀላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም የአሜሪካ የወጪ ጉዳይ መስሪያ አስታውቋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የፖለቲካና የፀጥታ አማካሪ በመሆን በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት፣ በተለይም በሶሪያና ሊባኖስ ጦርነት ቆሞ ሰላም እንዲመጣ በተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ዋና ልዑክ በመሆን ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማን፣ ተልዕኳቸውን ጀምረው ረቡዕ ዕለት ከግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ተወያይተዋል።
ፊልትማን እና አልሲሲ በካይሮ:-
በውይይቱ ወቅት፣ አብዱልፈታህ አልሲሲ “አሜሪካ በግድቡ ምክንያት ለተነሳው ውዝግብ መፍትሄ ለማግኘት ውጤታማ ሚና እንድትጫወት” መጠየቃቸውና ግድቡ የሃገራቸው የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረው፣ ግብጽ የውሃ ፍላጎቷን የሚጎዳ ከሆነ ማንንም እንደማትቀበል ማስታወቃቸው ተሰምቷል።
በተጨማሪ ፌልትማን፣ የግብጹን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያነጋገሩ ሲሆን፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጥንቃቄ ለሚፈልገው ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ለመሻት ከልብ እንዳሰበበት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ሴናተሮች ከሱዳን መሪዎች ጋር:-
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተሰየመውና በልዩ መልዕክተኛው ፊልትማን የሚመራው ልዑካን ቡድን አባል የሆኑት፣ በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባሉ ሴናተር ክሪስ ኩን የተመራ ልዑክ ከሱዳን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብደላ ሃምዶክ እና ከአብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር በካርቱም ውይይት አድርጓል።
አሜሪካ የሱዳንን የሽግግር መንግስት እንደምትደግፍ ሴናተር ክሪስ ኩን ማረጋገጣቸውን በመጥቀስ ሱናን የተሰኘው የሀገሪቱ ሚዲያ እንደገለፀው፣ ከውይይቱ በኃላ ሴናተር ኩንስ በሰጡት አስተያየት “አሜሪካ እሰካሁን 700 ሚልዮን ዶላር ለሱዳን ድጋፍ እንዳደረገች በመግለፅ በቀጣይ ለሱዳናውያንን ሁለንተናዊ መረጋጋት፣ ደህንነትና ሰላም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች” ብለዋል።
የልዑኩ ሌላኛው አባል ሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን በበኩላቸው፣ በሱዳን ያለውን ሽግግር በማድነቅና ሱዳን ወደ ዴሞክራሲ፣ ሰላም እና ፍትህ ለምታደርገው ጉዞ አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ፤ ከሱዳን መንግስት ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት መግለጫ “ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን ለፈለገችው ልማት የመጠቀም መብት አላት” ማለታቸው ተሰምቷል።
ሴናተሩ ካርቱም ሆነው በሰጡት በዚሁ መግለጫ “አሜሪካ የሦስቱንም ሀገሮች ፈቃደኝነት ሳታገኝ በግድቡ ዙሪያ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የላትም” በማለት ገልፀው፣ ሦስቱም አገሮች ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ግን አሜሪካ ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።
ፌልትማን ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ጋር:-
በጄፍሪ ፌልትማን የሚመራው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ልዩ ልዑክ ኤርትራ አስመራ ገብተው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈረወርቂ ጋር “በደንደን የእንግዳ መቀበያ” መነጋገራቸው ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በውይይቱ ወቅት “ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ከአሜሪካ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት” ማለታቸውን የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ የማነ ገ/መስቀል በይፋዊ ትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።
አምባሳደር ፌልትማን በበኩላቸው፣ በአፍሪካ ቀንድ እየታዩ ባሉ ችግሮች ዙሪያ የአሜሪካ አስተዳደር ያለውን አመለካከትና እይታ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንዳብራሩላቸው የኤርትራው ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ገልፀዋል።
የነበረው ውይይት 4:00 ሰዓት ገደማ የወሰደ እንደነበረ የተሰማ ሲሆን፣ ከላይ ከተገለፀው ውጭ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች እስካሁን ይፋ አልሆኑም።
ዴቪድ ሺን ምን እያሉ ነው?
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና አሁን ላይ በአሜሪካ ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የውጭ ግንኙነቶች መምህር የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሺን፣ የአገራቸው መንግስት “ኢትዮጵያን የማገዝ ኤርትራን ግን የመቅጣት ፍላጎት እንዳለው” የሚያሳብቅ መረጃ ከአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሾልከዋል።
“አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ እንዲያስቆምና ክልሉን መልሶ ለመገንባት እንዲችል እየጣረች ነው ያንን ለማድረግ የሚያስችል የማማከርና የሰብዓዊ ርዳታ እየሰጠች ነው” ያሉት ዴቪድ ሺን “አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ አትፈልግም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህዝብ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ መኖራቸውን ይቀበላሉ ብለው እንደማያስቡ የገለፁት አምባሳደሩ፣ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ መኖራቸው ሉዓላዊነትን የሚፈታተን መሆኑን ገልፀው፣ ወታደሮቹ በአስቸኳይ ወደ ኤርትራ መመለሳቸው የኢትዮጵያም፣ የአሜሪካም፣ የኤርትራም ፍላጎት እንደሆነ እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
“የኤርትራ ወታደሮች የማይመለሱ ከሆነ አሜሪካ ኤርትራን በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ተቀባይነት የሌላት ሀገር አድርጋ ልትቆጥራት ትችላለች” በማለትም የአገራቸውን መንግስት ቀጣይ አካሄድ አመላክተዋል።
አምባሳደር ዴቪድ ሺን “አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ አትፈልግም” በማለት የገለፁት የአገራቸው መንግስት አቋም፣ በአንዳንዶች ዘንድ ይህ አቋም በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ የልዑካን ቡድን ላይም የተንፀባረቀ መሆኑ እየተጠቀሰ የሚገኝ ሲሆን፣
ሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን ከካርቱም በሰጡት መግለጫ “ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን ለፈለገችው ልማት የመጠቀም መብት አላት” ማለታቸውም “የዚሁ መንግስታዊ አቋም ነፀብራቅ ነው” ተብሎ እየተጠቀሰ ይገኛል።
ኤርትራ እና ሱዳን ምን መከሩ?
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ለ2 ቀን የስራ ጉብኝት ወደ ካርቱም አምርተው ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና አማካሪያቸው ጋር ውይይት በማድረግ መመለሳቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሱዳን ትሪብዩን አስነብቧል።
በሱዳንም በኤርትራም በኩል ከወጡት መግለጫዎች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ የሀገራቱ ውይይት እና ንግግር ትኩረት ያደረገው በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ላይ አተኩረው ባደረጉት ውይይት የሱዳን እና የኤርትራን ግንኙነት ለማጠናከር ከስምምነት ደርሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኢሳያስ ከአል ቡርሃን በተጨማሪ፣ ከዶ/ር አብደላ ሃምዶክ ጋር በተናጠል የተወያዩ ሲሆን፣ “የቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደት የፖለቲካ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያስችል መንገድ ያመቻቻል” በሚል መስማማታቸው ከሱዳን በኩል ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያሳ ወደካርቱም ከመሄዳቸው ቀደም ብሎ ከካርቱም የወጡ በርካታ ሪፖርቶች “በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ያሸማግላሉ” ሲሉ የነበረ ቢሆንም እስካሁን በዚህ ጉዳይ ምንም የተባለ ነገር የለም።
ይሁንና፣ የፕሬዝዳንት ኢሳያሳ የካርቱም ጉብኝት ዋና አላማ እየተባባሰ ከመጣው የኢትዮ ሱዳን ውዝግብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የጠቀሱ ምንጮች፣ የኤርትራ ወዳጅና ስፖንሰር የሆኑት እንዲሁም “በትግራዩ ጦርነት ኤርትራ ኢትዮጵያን እንድታግዝ አድርገዋል የሚባሉት” የአቡዳቢው ልዑል ቢንዛይድ፣ ከቀናት በፊት በግብጽ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ ፕ/ት ኢሳያስ ወደሱዳን ማቅናታቸውን፣ የጉዞው ዓላማም ኢትዮ ሱዳንን የማስማማትና ይህም በሚስጥር እንዲያዝ መስማማታቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ነገ ወቅታዊ ሪፖርታዥ ምን ብሏል?
ከቀናት በፊት “ኢትዮጵያ የአቡዳቢ ልዑል ካይሮን ከጎበኙ በኋላ በግድቡ ጉዳይ የሱዳንና ግብፅ ህብረት እየላላ መሆኑ ተነገረ፤ ሱዳን ወደድርድሩ መመለስን፣ ግብፅ በቀደመ ሴራዋ መቀጠልን መርጠዋል” በሚል በኢትዮጵያ ነገ በቀረበ ወቅታዊ ሪፖርታዥ “የአቡዳቢ ገዥ የሆኑት ልዑል አልጋ ወራሽ ሼኽ መሐመድ ቢን ዛይድ፣ በግብፅ ያደረጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ተከትሎ ግብፅና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ያሳዩ የነበረው ህብረት በፍጥነት እየላላ መሆኑና ሁለቱ አገራት በተከታታይ የተናጠል አቋሞችን ማንፀባረቅ መጀመራቸው፣ መጋቢት ላይ ኢትዮጵያና ሱዳንን የማሸማገል ጥሪ ከአቡዳቢ ሲቀርብ ለግብጾች መርዶ መሆኑን የካይሮ ልሂቃን በርካታ የደህንነት መረጃዎች በአስረጂነት ጠቅሰው ሲገልፁ እንደነበር በተለይም ኤምሬትስ ከእስራኤል ጋር ዕርቅ ማውረዷን ተከትሎ የእስራኤሉ ሞሳድ በሱዳን መንግስትና በናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ ፈላጭ የሚሆንበት ጅምር መታየቱ እስራኤልና ኤምሬትስ ግብፅን ክፉኛ የሚጎዳውን የውሃ ካናል በደቡባዊ ቀይ ባህር ኤልያትና ሃይፋ መካከል ለመገንባት ስራ መጀመራቸውን አመላካች እንደሆነና ይባስ ብሎም ቢን ዛይድ ከሱዳን ጋር ለሳምንታት ከመከሩ በኋላ ወደ ካይሮ ያቀኑት የሱዳኑ ጦር መሪ አልቡርሃን ከግብፅ ጋር የፈጠሩትን ጥምረት ለመበጠስ ስለመሆኑ የደህንነት ምንጮችን ዋቢ ያደረጉ ትንተናዎች መጠቆማቸው እንዲሁም አልሲሲ እና ቢንዛይድ ያደረጉት ምክክር በሁለታቸው መካከል ሌላ ባለስልጣን በሌለበት መሆኑም ለጉዳዩ ከባድነት ማጠናከሪያ እንደሚሆንና የግብፁ “ዲግኒቲ ፓርቲ” መሪ አህመድ ታንታዊ የልዑሉን ጉብኝት ተከትሎ “ኤምሬትስ ለግብፅ ቁልፍ ስጋት በሆነው የግድቡ ጉዳይ ያሳየችው ግዴለሽነት ለካይሮ አደገኛ ነው” ሲለማለታቸው በሰፊው መተንተኑ ይታወሳል።
በዚሁ በኢትዮጵያ ነገ በቀረበ ወቅታዊ ሪፖርታዥ “ቀደም ሲል ከግብፅ ጋር ተመሳሳይ አቋም ስታራምድ የቆየችው ሱዳን፣ ባልተጠበቀ መልኩ “ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ያሉ ልዩነቶች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ይፈታሉ የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ” ማለቷ በሁለቱ አገራት መካከል በግድቡ ጉዳይ የነበረው ህብረት እየላላ መሆኑ ማሳያ መሆኑና ይህም ልዩነት የአቡዳቢው ልዑል ካይሮን ከጎበኙ በኋላ እየሰፋ መምጣቱ” የተገለፀ ሲሆን፣ ፕ/ት ኢሳያስ ወደ ካርቱም ያቀኑት ሱዳን ይህን አቋም በገለፀት ማግስት መሆኑም የኢሳያስ አፈወርቂን የጉዞ አላማ እንደሚያመላክት ተነግሯል።