በኢትዮጵያ የጎርፍ አደጋ በህይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው!

በኢትዮጵያ የጎርፍ አደጋ በህይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- በሶማሌ ክልል የአፍዴር ዞን በራሶ፣ ዶሎባይና በባሬይ ወረዳዎች በተከታታይ በጣለ ከባድ ዝናብ የ7 ህይወት ማለፉ፣ የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት በምዕራብ ኢሜይ ወረዳ እና  አካባቢዎች 1,383 አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውና በዘንድሮ በደረሰ የሰብል ምርት ላይ ጉዳት መድረሱን የዞኑ አስተዳዳሪ  አቶ ሹክሪ ሀሰን አስታውቀዋል።

እንዲሁም፣ በዚያው በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ሺኒሌ ወረዳ በጣለ ከባድ ዝናብ፣ መርማርሳ የተባለው ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ የአንድ አርብቶ አደር እናት ህይወት ማለፉና ሲጠብቋቸው የነበሩ በርከት ያሉ ፍየሎችም በጎርፉ መወሰዳቸውን የሺኒሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን አደም አስታውቀዋል።

በወረዳው በጣለው ዝናብና ወንዙ ሞልቶ ባደረሰው የጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን እናት አስከሬን የማፈላለግ ተግባር አካባቢው የፀጥታ አካላት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት የወረዳው አስተዳዳሪ፣
የጎርፍ አደጋው በቅርቡ በአካባቢው ተወላጅ ዲያስፖራና በክልሉ ባለሃብቶች የተገነቡና ማህበረሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ማፈራረሱንና ጉዳት ማድረሱንም አመልክተዋል።

ሺኒሌ ከተማና ድሬዳዋን የሚያስተሳስረውን የአስፋልት መንገድም በጎርፉ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን በመግለፅም የአካባቢው ህብረተሰብ በቀጣዩ ቀናት ሊጥል የሚችለው  ዝናብን ተከትሎ ሊከሰቱ  ከሚችሉ የጎርፍ አደጋዎች ጥንቃቄ እንዲያደርግና ከወንዝና ተፋሰስ አካባቢዎች እንዲርቅ የወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን አደም አሳስበዋል።

በተያያዘ፣ በድሬዳዋ ቀበሌ 08 ልዩ ስሙ “ለገሃሬ ከመንገድ በላይ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት  ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ፣ የአንድ መኖሪያ ቤት አጥር ግንብ ፈርሶ በመኖሪያ ቤት ላይ በመውደቁ፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 3 ሰዎች
ህይወት ማለፉና በመብረቅ አደጋም አንድ ሰው መሞቱ ተገልጿል።

ህይወታቸው ያለፈው የ12 አመት፣ የ3 አመት እና የ2 ወር ህጻን ልጅ መሆናቸውንና የልጆቹ ወላጅ እናት እና አንድ ወንድ ልጃቸው ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ድሬዳዋ ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኙ የገለፀው የድሬዳዋ ፖሊስ፣ በልጆቹ አባት ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱንም አስታውቋል።

በሌላ በኩል፣ በከተማዋ ቀበሌ 01 “መልካ ጀብዱ” ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት የኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ግቢ ውስጥ በስራ ላይ በነበሩ ሁለት ግለሰቦች ላይ መብረቅ ወድቆ በአንደኛው ግለሰብ ላይ የሞት አደጋ ሲያስከትል፣ በሌላው ግለሰብ ላይ የአካል ጉዳት መድረሱና ግለሰቡ በማርያም ወርቅ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት መሆኑ ተገልጿል።

ባለፈው ሚያዝያ 24/2013 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የአንድ ድርጅት አጥር ፈርሶ በአደጋው የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ “በቀጣይ ቀናት ዝናብ ጥሎ የጎርፍ አደጋ ሊደርስ ስለሚችል ህብረተሰቡ ተገቢው ጥንቃቄ ሊያደረግ ይገባል” በማለት ያሳሰበው የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፣ በቀሪው የበልግ ወቅት
በምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ አርሲ፣ ቦረና፣ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል የጎርፍ ስጋት መኖሩን ጠቁሟል።

እንደ ብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ሁኔታ ትንበያ ከሆነ፤ በሶማሌ ክልል፦ ሸበሌ፣ አፍዴር፣ ሊበን፣ ዶሎ፣ ፋፋን፣ ሲቲ፣ ዳዋና አካባቢዎች፣ በደቡብ ክልል፦ በሀዲያ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በዳውሮ፣ በሰገን፣ በስልጤ፣ ጉራጌና አንዳንድ አካባቢዎች፣ በሲዳማ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችናበድሬዳዋ ከተማና የገጠር ቀበሌዎች ወቅቱን ካልጠበቀው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የጎርፍ አደጋ በሰዎችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተገምቷል።

LEAVE A REPLY