ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- በአዳማ ከተማ ከሚያዝያ 27 እስከ 29/2013 ዓ.ም ለሶስት ቀናት በተደረገ ፍተሻ፣ 10 M1 የጦር መሳሪያ፣ 9 የተለያዩ ሽጉጦች፣ 1 የእጅ ቦምብ እና 1 ክላሽ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
የከተማው ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ፣ የጦር መሳሪያዎቹ ቦሌ፣ ቦኩ እና አባገዳ በተባሉት ክፍለ ከተሞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ 6 ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተያያዘ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በተደረገ ክትትል በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 110 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረው ዶላር የተያዘው ሚያዚያ 28 ለ29 አጥቢያ 2013 ዓ/ም በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ላምበረት ተብሎ በሚጠራው መናኸሪያ ግቢ ውስጥ በግምት ከለሊቱ 10 ሰዓት ከ40 ደቂቃ መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከህዝብ በተገኘ ጥቆማ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቅንጅት ባደረጉት ክትትል ከአዲስ አበባ ወደ ሃረር ሊጓዙ የተዘጋጁ ሁለት ተጠርጣሪዎች በያዙት ሻንጣ ላይ በተደረገ ፍተሻ፣ በጥቁር ላስቲክ የተጠቀለለ 110 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሊገኝ መቻሉንና ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡