ሱዳን በግድቡ ዙሪያ እና በድንበሩ ጉዳይ የምታነሳው ጥያቄ የሶስተኛ ወገን ፍላጎት እንዳለበት...

ሱዳን በግድቡ ዙሪያ እና በድንበሩ ጉዳይ የምታነሳው ጥያቄ የሶስተኛ ወገን ፍላጎት እንዳለበት ተገለፀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ በምክንያታዊነትና በፍትሃዊነት በጋራ የመጠቀም መብት አክብራ እየሰራች እንደሆነ የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ በሱዳን በኩል በግድቡ ዙሪያ እና በድንበሩ ጉዳይ የሚነሳው ጥያቄ የሚያመለክተው የሶስተኛ ወገን ፍላጎት ያለበት መሆኑን እንደሆነ ገልጸዋል።

በሱዳንና ግብፅ በኩል ጉዳዩ አለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው የማድረግ እንቅስቃሴ መኖሩን፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ፣ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የዉሃ ሙሌት ጀምሮ መረጃ ለመለዋወጥ ያላትን ፍቃደኛነት መግለጿን፣ አሁንም ሀገራቱ  ባለሙያዎችን በመሰየም የሁለተኛው ዙር የግድቡን የዉሃ ሙሌትን በተመለከተ አስፈላጊው መረጃ መለዋወጥ እንዲቻል ያላትን ፍላጎት ቀደም ሲል ለሀገራቱ በይፋ ማሳወቋን፣ ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች፤ አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለው መርህ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ያላትን ፍላጎት በተለያየ መንገዶች እየገለጸች እንደምትገኝና ከአባይ ውሃ 86 ከመቶ በላይ የምታመነጭ ሀገር በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ ስምምነቶች አሁንም ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የመጠቀም ተግባር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኢትዮጵያ ስትገልጽ መቆየቷን ያስታወሱት አምባሳደር ዲና፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተም የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ረጅም ዘመን የተሻገር መሆኑንና በመሪዎች እንዲሁም በጋራ የድንበር ኮሚቴዎች ደረጃ በተለያየ ጊዜ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

“ሱዳን በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የተከናወነው የህግ ማስከበር ዘመቻን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ልዑላዊ ግዛትን በመውረር የቁስ እና ሰብዓዊ ሀብት ውድመት አድርሳለች” ሲሉ አያይዘው የገለፁት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “የግድቡ ግንባታ ሂደት እና ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በታቀደለት ጊዜ ይከናወናል” በማለትም አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY