ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- የአውሮፓ ሕብረት የውጪ ጉዳዮች እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል፣ ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ “ህብረቱ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ለመላክ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚሰማራበት ቁልፍ መለኪያዎች (ፓራሜትርስ) ላይ ከስምምነት መድረስ አልተቻለም፣ የአውሮፓ ሕብረት የዲሞክራሲ ግንባታ ድጋፍ ዋናው ምሰሶ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ትክክለኛነት ነው። ሕብረቱ የምርጫ ታዛቢ ልዑኩን ለመላክ ያቀረባቸው መስፈርቶች እንዳይሟሉ መከልከሉ አሳዝኖኛል” በማለት ሕብረቱ ታዛቢዎችን የመላክ እቅዱን አንደሰረዘ የተናገሩ ቢሆንም፣ አሁን ግን ምርጫውን የሚታዘቡ ኤክስፐርቶች የመላክ ፍላጎት እንዳለው ማሳወቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልፀዋል።
ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የ6ኛውን ብሔራዊ ምርጫ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሂደቱን በተሟላ መልኩ እያካሄደ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ምርጫውን ለመታዘብ ጥያቄ ያቀረቡ የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ ተቋማት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚሁ መግለጫቸው “የመታዘብ ሂደቱ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በኩል የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የሚፈጸም ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በተያያዘ፣ ማንኛውም ገለልተኛ አገር አቀፍ ወይም ዓለም አቀፍ ታዛቢ የኢትዮጵያን ምርጫ ለመታዘብ በቅድሚያ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ሊያከብሩ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገልጿል፡፡
“ምርጫን የመታዘብ ጉዳይ የሀገሪቱን ሕገመንግሥት ማዕቀፍ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት” ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ፣ መንግሥት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማይጻረር መልኩ ከታዛቢዎች ጋር ተነጋግሮ ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚገባ ጠቅሶ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት ምርጫውን ላለመታዘብ የመወሰን ወይም አለመፈለግ መብቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንደሚያከብር ያመለከተው መግለጫው “ሕብረቱ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ የይስሙላ ምርጫዎችን ሲታዘብ ኖሮ በዘንድሮው ምርጫ ከታዛቢነት ለመውጣት የወሰነበትን ምክንያትና ያልተግባባበትን ነጥብ ለባለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ አለበት” ብሏል።
በሌላ በኩል “የአውሮፓ ህብረት ነፃ ፉክክር፣ ነፃ ሚዲያ እና ነፃ የምርጫ ቦርድ ባልነበረበት ባለፉት ምርጫዎች ይታዘብ የነበረው ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ተቆርቋሪ ሆኖ አልነበረም” ሲሉ አንጋፋው ፖለቲከኛና የኢሳት ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ተናግረዋል።
“ሕብረቱ ታዛቢዎችን ላለመላክ የወሰነው፣ ለሕብረቱ ሀገራት የማይታዘዝና የማያጎበድድ መንግሥት ይመጣል የሚል ስጋት ስላለው ነው” ያሉት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ “የአውሮፓ ህብረት ከዚህ ቀደም በነበሩት ምርጫዎች ታዛቢዎችን ልኮ ምርጫ ሲታዘብ የነበረው በዕርዳታ ሰበብ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበት ዕድል ስለተፈጠረለት ነው። በአሁኑ ወቅት ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ነፃነት ባለበት ሁኔታ ምርጫ የምታካሂድ በመሆኑ ለእነሱ የማይታዘዝና ለሃሳባቸው የማይንበረከክ መንግሥት ይመጣል የሚል ስጋት ስላለባቸው ከታዛቢነት ሚናቸው ለማፈግፈግ ወስነዋል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
“ባለፉት አምስት ምርጫዎች ዕርዳታ ለማግኘት ሲባል በሀገራችን ላይ ፈላጭ ቆራጭ አንዲሆኑ ፈቅደንላቸዋል” በማለት በተለይም ህወሓት ሀገሪቱን በሚያስተዳደርበት ወቅት እነዚህ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበርና ይህም ለእነሱ የአሽከርነት ሚና የሚጫወት መንግሥት ለመፍጠር ያስቻላቸው መሆኑንም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አመልክተዋል።