የአሜሪካ ሴናተሮች በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ያቀረቡት አዲስ ሃሳብ በምርጫ ቦርድ ውድቅ...

የአሜሪካ ሴናተሮች በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ያቀረቡት አዲስ ሃሳብ በምርጫ ቦርድ ውድቅ ሆነ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– መጭው ሀገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የአሜሪካ ሴናተሮች እና የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሬይ ፌልትማን ምርጫውን ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ግልጽ ለማድረግ ምርጫን በማራዘም መሠረታዊ ለውጥ እንዲካሄድ ያቀረቡትን ሀሳብ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዳብዳቤ መልስ ሰጥቷል፡፡

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ እና ፍትሐዊ ለማድረግ አሳታፊ በሆነ መንገድ እየተሠራ መሆኑንም ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ “ግንቦት 28/2013 ዓ.ም የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የምርጫ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉበት ነው” ብሏል።

ለዚህም ሕጋዊ ፍቃድ ካላቸው 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 48 ፓርቲዎችን የወከሉ 9 ሺህ እጩዎች መቅረባቸውን እና ከ190 በላይ ሀገር አቀፍ የሲቪክ ድርጅቶች ትምህርት መስጠታቸውን፣ 32 ሀገር አቀፍ ተቋማት ምርጫውን ለመታዘብ ፍቃድ መውሰዳቸውን የገለጸው የቦርዱ ምላሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎቻቸው በምርጫው ሂደት ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውንና ከ100 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምርጫውን ለማስተባበር በመንቀሳቀሰ ላይ እንደሚገኙ የገለፀው የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ “6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ በግልጽነት እየተመራ ነው” ሲልም አመልክቷል።

“ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ከምንጊዜውም በላይ ጥረት ተደርጓል” ሲል የገለፀው የምርጫ ቦርድ ምላሽ “በመሆኑም 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በአዲስ ሪፎርም ለማስኬድ የቀረበው ሃሳብ ከወጪም ሆነ ከጊዜ አንፃር የሚያስኬድ አይደለም” በማለትም የአሜሪካ ሴናተሮች ምርጫን በማራዘም መሠረታዊ ለውጥ እንዲካሄድ ያቀረቡትን ሀሳብ ውድቅ አድርጎታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከሚያዚያ 26/2013 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ልዩ መልዕክተኛው ትናንት ኢትዮጵያ መግባታቸውና ዛሬ ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።

በግድቡ ግንባታና የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ዛሬ  በሚኒስትሩ ሰፊ ገለፃ የተደረገላቸው ጄፍሬይ ፌልትማን፣ ከኢትዮጵያ በፊት በግብጽ፣ በሱዳን እና ኤርትራ ጉብኝት አድርገው ከሀገራቱ መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ ትብብርና ቀጣናዊ ጉዳዮች መምከራቸው የሚታወስ ነው።

ልዩ መልእክተኛው እስከ ግንቦት 5/2013 ዓ.ም በአፍሪካ ሀገራት ከሚኖራቸው ቆይታ በተጨማሪ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከፖለቲካ አመራሮችና ከሰብዓዊ እርዳታ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉም ተብሏል።

የ62 ዓመቱ ዲፕሎማት፣ ከ1986 (እ.አ.አ) አንስቶ በተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አሜሪካን ወክለው ያገለገሉ ሲሆን፣ የአፍሪካ ቀንድ ጉብኝታቸውን በሚመለከት ባለፈው ዓርብ ልዩ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

LEAVE A REPLY