የአቡነ ማቲያስ መልዕክት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱ ተመለከተ!

የአቡነ ማቲያስ መልዕክት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱ ተመለከተ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፅዑ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ከቀናት በፊት በስልክ የተቀረጸ የቪዲዮ መልእክታቸው በትግራይ ሚዲያ ሀውስ (TMH)፣ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጽሁፋቸው ደግሞ በአሶሺየትድ ኘሬስ (AP) መለቀቁና በመልዕክቱ ያነሱት ጠንካራ ሀሳብ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱን ለመረዳት ተችሏል።

ቅዱስነታቸው፣ በተለይም በትግራይ ጉዳይ በሰጡት አስተያየት የትግራይ ሕዝብ ላይ እልቂትና ብዙ ወንጀል እየተፈጸመ መሆኑን መናገራቸውና ይህንን ሐሳባቸውን ለማካፈልም ብዙ ጊዜ ሞክረው ሀሳባቸውን እንዳያጋሩ መታፈናቸውንም ይፋ ማድረጋቸው አሁን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ለተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፣ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስም “ፓትርያሪኩ ያስተላለፉት መልዕክት የግላቸው እንጂ የቤተክርስቲያኗ አቋም አይደለም” ሲል ዛሬ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፅዑ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ሰሞኑን የተናገሩት እና በማኀበራዊ መገናኛዎች ሲዘዋወር የነበረው ሃሳብ የግላቸው እንጂ የቤተክርስቲያኗ አቋም አለመሆኑን በመግለጽ “በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ችግር ሲፈጠር ቅዱስ ሲኖዶሱ ተወያይቶ መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል፤ እየሰጠም ነው፤ እርዳታም ተደርጓል” ሲሉ የተናገሩት የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ናቸው፡፡

“አቡነ ማትያስ ተናገሩት ተብሎ በማኀበራዊ መገናኛዎች የተሰራጨው ንግግር ቅዱስ ሲኖዶሱ ያልተወያየበት እና ያልወሰነው ጉዳይ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱን የማይወክል ሀሳብ ነው” ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ በቀጣይ ጉዳዩ ላይ ለመነጋገር አጀንዳ መያዙንና ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚወያይበት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በተያያዘ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን በመኖሪያ ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን ኤምባሲው አስታውቋል።

ውይይታቸው ፓትሪያርኩ ሰሞኑን በይፋ ያስተላለፉትን መልዕክት ጨምሮ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ እና በተለይም በትግራይ ስላለው የሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን የጠቀሰው ኤምባሲው፣ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ወደፊት በኤምባሲው በሚካሄዱ እና የተለያዩ የእምነት ተቋማት በሚሳተፉባቸው የማህበረሰብ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ውይይታቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ ፓትሪያርኩን መጋበዛቸውንም አመልክቷል።

LEAVE A REPLY