የአውሮፓ ሕብረት፣ 2 የአሜሪካና አንድ የሩሲያ ተቋማት የምርጫ ታዛቢ እንደሚልኩ ተገለፀ!

የአውሮፓ ሕብረት፣ 2 የአሜሪካና አንድ የሩሲያ ተቋማት የምርጫ ታዛቢ እንደሚልኩ ተገለፀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሁለት የአሜሪካ ተቋማትና አንድ የሩሲያ ተቋም እንደሚታዘቡ፣ የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢ ባለሙያዎችን ለመላክ እንደተስማማና የአፍሪካ ሕብረትም ምርጫውን እንደሚታዘብ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

አያይዘውም፣ በሳምንቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታና በቀጣናው ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩ ሲሆን “ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት እሳቤን በመደገፍ ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

የኮሞሮስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን፣ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሬይሪ ፊልትማን ጋር በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር፣ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ መወያየታቸውን፣ እንዲሁም
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፊልክስ ሲሼክዲ በግድቡ የድርድር ሂደት ላይ ለመምከር አዲስ አበባ መግባታቸውንም ቃለ አቀባዩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአፈሪካ ህብረት ሊቀመንበርን አዲስ አበባ  መግባት ተከትሎ በፌስ ቡክ ገፃቸው ፡ –

ወንድሜ ፕሬዚደንት ፊሊክስ ቲሼኬዲ እንኳን በሰላም ወደ ኢትዮጵያ መጡ። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር አዎንታዊ ውጤት እንዲያስገኝ ስለሚያደርጉት በጎ አስተዋጽዖ አመሰግናለሁ። ኢትዮጵያ ለሁሉም አስፈላጊ እና ጠቃሚ ወደ ሚሆን ስምምነት ለመድረስ፣ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን ሂደት ለመከተል ባላት ቁርጠኝነት ትቀጥላለች። የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

LEAVE A REPLY