ለአገራዊ ምርጫው ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉና በመላ ሀገሪቱ በአንድ ቀን እንዲካሄድ መወሰኑ ተገለፀ!

ለአገራዊ ምርጫው ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉና በመላ ሀገሪቱ በአንድ ቀን እንዲካሄድ መወሰኑ ተገለፀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ከተያዘለት ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ተጨማሪ ሁለትና ሶስት ሳምንት ጊዜ እንደሚያስፈልግ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ምርጫው በተመሳሳይ ቀን እንዲካሄድ መወሰኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡

በሀገር አቀፍ ምርጫው፣ የመራጮች የምዝገባ እና የቀጣይ የምርጫ ሂደት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ዛሬ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ምርጫው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተመሳሳይ ቀን እንዲካሄድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ የውይይት መድረክ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ምርጫው በአንድ ቀን እንዲካሄድ መወሰኑን ያስታወቁት የቦርዱ ሊቀ መንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት ጊዜ አለመከናወኑና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ አለመካሄዱን ገልፀው፣ የመራጮች ምዝገባው መዘግየትም የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ስራውን በ10 ቀናት እንዲዘገይ ማድረጉንና ይህም ለድምጽ መስጫው ቀን መራዘም ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህን ምክንያቶች ተከትሎም ለድምጽ መስጫው ቀን የሚያስፈልጉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ማካሄድ እንዳልተቻለ እና ድምጽ አሰጣጡ በተመሳሳይ ቀን እንዲሆን ከውሳኔ የተደረሰውም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ከፓርቲዎች በቀረበው ጥያቄ መሰረት መሆኑን አያይዘው የጠቀሱት ሊቀ መንበሯ፣ ምርጫውን ለማስፈጸም የሚያግዙ ያልተከናወኑ ሥራዎች በመኖራቸው፣ ምርጫውን ለማካሄድ የተወሰኑ ቀናቶችን ማራዘም ማስፈለጉ ግልጽ አድርገዋል፡፡

በዛሬው የውይይት መድረክ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ የምርጫው መራዘም አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፣ በምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች ግን ምርጫ ቦርዱ በአስቸኳይ መፍታት እንዳለበት ማሳሰባቸውን ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY