ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- የኢትዮጵያ ብሄራዊ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን አባላት የማበረታቻና ሽልማት ፕሮግራም በሀዋሳ ተካሄዷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ማለፋን ተከትሎ ነው የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በጋራ የእውቅናና የማበረታቻ ፕሮግራሙን ያዘጋጁት።
በፕሮግራሙ ላይ ለብሄራዊ ቡድኑ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ማበረታቻ እንደተደረገለት ኮሚሽኑ ገልጿል። ለዋና አሠልጣኝ 350ሺ፣ለረዳት አሠልጣኞች ለእያንዳንዳቸው 250 ሺ ፣ለቋሚ ተሰላፊዎች ለእያንዳንዳቸው 250 ሺ፣ ለ5ተቀያሪ ተጨዋቾች ለእያንዳንዳቸው 150 ሺ ፣ለኮችንግ ስታፍ አባላት ለእያንዳንዳቸው 100 ሺ እና ለሌሎችም በየደረጃው ማበረታቻ ተደርጎላቸዋል።
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች አቡበከር ናስር በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል የማስቆጠር ሪከርድ መስበሩ ታውቋል፡፡
አቡበከር ናስር፣ ትናንት በነበረው ጨዋታ፤ ሲዳማ ቡና ላይ በ9ኛው፣ 36ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው 3 ግቦች የውድድር ዘመኑ ጎሎቹን ቁጥር 27 ያደረሰ ሲሆን፣ በዚህም በጌታነህ ከበደ በ2009 ተይዞ የነበረውን በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል የማስቆጠር ሪከርድ ከወዲሁ ማሻሻሉን ለማወቅ ተችሏል።