በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ሽቦ ስርቆት ሲፈፅሙ የነበሩ 10 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ!

በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ሽቦ ስርቆት ሲፈፅሙ የነበሩ 10 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናበአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ አብነት፣ ዳርማር፣ ልደታ እና ተግባረ-ዕድ በተባሉት አካባቢዎች የባቡር ፌርማታዎችን ተገን አድርገው የኤሌክትሪክ ሽቦ ስርቆት ሲፈፅሙ የነበሩ 10 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታውቋል!

ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ከአብነት የባቡር ፌርማታ ላይ ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ ሽቦ ሲቆርጥ በፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ ከተያዘ አንድ ተጠርጣሪ በመነሳትና የምርመራ ቡድን በማቋቋም የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ያመለከተው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በዚህም በተለያየ ጊዜ በባቡር መስመሩ ላይ ወንጀል ሲፈጽሙ እና የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ እንዲስተጓጎል ሲያደርጉ የነበሩ ተጨማሪ 9 ተጠርጣሪዎች እና ግምቱ ከ1 ሚሊዮን 564 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ተሰርቆ የተቆራረጠ የባቡር መስመር የኤሌክትሪክ ሽቦ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

“ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከልም 4ቱ በዋና ወንጀል ፈጻሚነት፣ 2ቱ የተሰረቀውን ሽቦ የሚያመላልሱ የላዳ ታክሲ አሽከርካሪዎች፣ 3ቱ የተሰረቀውን ሽቦ የሚቀበሉ ሲሆኑ፣ 1 ተጠርጣሪ ደግሞ ለሌላኛው ተጠርጣሪ ሀሰተኛ መታወቂያ እንዲዘጋጅ ያደረገ ነው” ያለው የከተማዋ ፖሊስ፣ በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያናጉ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ሊጠብቃቸው እንደሚገባ አሳስቦ፣ በተለይም የምድር ባቡሩ የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንደ ግል ንብረቱ ሊጠብቅና አጠራጣሪ ነገሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት ጥቆማ ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክቷል።

LEAVE A REPLY