ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ በማስመልከት ሰሞኑን ያሳለፈውን የውሳኔ ሐሳብ “ኢፍትሐዊና በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት እና ሉዓላዊነትን ያለመጣስ የተባበሩት መንግሥታት መርህን የሚቃረን ነው” ሲል የአማራ ምሁራን መማክርት አውግዞታል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በኩል የተላለፈው የሴኔቱ የውሳኔ ሐሳብ “በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ህወሓት እና ሌሎች የግጭቱ ተሳታፊዎች ግጭቱን እንዲያቆሙ፣ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲፈቀድ፣
እንዲሁም ግጭቱን ተከትሎ ተዓማኒ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ትብብር ያድርጉ” ሲል የጠየቀ ሲሆን፣ የአማራ መማክርት ጉባኤ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ውሳኔውን “ኢፍትሐዊ እና ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የሚጥስ” ሲል ገልጾታል፡፡
መማክርቱ በዚሁ መግለጫው፣ አሸባሪው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢዎች ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ሲያካሂድ እንደነበር ጠቅሶ “በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን ሰሞኑን የተሰጠው መግለጫ ኢፍትሐዊና በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት እና ሉዓላዊነትን ያለመጣስ የተባበሩት መንግሥታት መርህን የሚቃረን ነው” ብሏል፡፡