በኤምባሲዎች በር ላይ ሊካሄድ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ተሰረዘ!

በኤምባሲዎች በር ላይ ሊካሄድ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ተሰረዘ!

“እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” የሚለው መርሃ ግብር በይፋ ተጀመረ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የውጭ ሀገራት መንግስታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ለማሳሰብ ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች መካከል፣ ዛሬ ሊከናወን የነበረው በኤምባሲዎች በር ላይ የኢትዮጵያዊያንን ድምጽ የማሰማትና ደብዳቤ ለማስገባት ፕሮግራም መሰረዙ ተገለፀ።

የተቃውሞ ሰልፎቹ አስተባባሪ ኮሚቴ ዛሬ ረፋድ ላይ በሰጠው መግለጫ “በተወካዮች በኩል የኢትዮጵያውያንን ድምጽ የያዘ ደብዳቤ ለማድረስ ቢታሰብም ኤንባሲዎች ዝግ በመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል” ብሏል።

“የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች መካከል ለኤምባሲዎች የኢትዮጵያውያንን አቋም የሚገልጽ ድበዳቤ በምንባብ በማሰማት መስጠት ነበር” ያለው አስተባባሪ ኮሚቴው፣ የዛሬ ዕቅድ ኤምባሲዎች ዝግ በመሆናቸው ባይሳካም ኤንባሲዎች ክፍት ሲሆኑ ደብዳቤው እንደሚሰጥ አመልክቶ “ከቀኑ 10 ሰአት ጀምሮ ግን መላ ኢትዮጵያውያን “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” የሚለው መርሃ ግብር በተያዘለት ጊዜ ይከናወናል” ሲል አስታውቋል።

ዛሬ ከረፋዱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ የኢትዮጵያዊያንን አቋም የሚገልፁት ደብዳቤዎች የማስገባት መርሃ ግብር በአሜሪካ ኤምባሲ፣ እንግሊዝ ኤምባሲ፣ ግብጽ ኤምባሲ፣ ሱዳን ኤምባሲና አውሮፓ ህብረት ደጃፍ ሊከናወን ዕቅድ መያዙን ከትናንት በስቲያ መዘገባችን ይታወሳል።

የአሜሪካ ኤምባሲም ትናንት በድረ ገፁ ባወጣው ማሳሰቢያ፣ ዛሬ አርብ የቆንስላ አገልግሎት እንደማይሰጥ ያሳወቀ ሲሆን፣ ኤምባሲው በአዲስ አበባ በሚገኙ በተለያዩ ኤምባሲዎች (የአሜሪካ ኤምባሲን ይጨምራል) የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጥሪ መቅረቡን እየተከታተለ መሆኑን በገለፀበት በዚሁ መግለጫው፣ በዚህ ምክንያትም ለደህንነት ጥንቃቄ ሲባል የቆንስላ አገልግሎት እንደማይሰጥ አሳውቆ አገልግሎት ፈላጊዎችም ወደ ኤምባሲው አካባቢ እንዳይጠጉ አስጠንቅቋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ፣ አሜሪካዊ ዜጎች ሚዲያዎችን እንዲከታተሉ፣ ሰዎች ከተሰበሰቡበት እና ከሰልፍ ቦታ እንዲርቁ፣ አካባቢያቸው እንዲቃኙ፣ በከተማይቱ ውስጥ ያላቸውን እንቅስቃሴ እንዲቀንሱ/እንዲቆጥቡ መልዕክት አስተላልፋለች።

በተያያዘ፣ በኢትዮጵያ እየደረሠ ያለውን ጫና በተመለከተ “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” የሚለው የተቃውሞ እንቀስቃሴ በመላው አዲስ አበባ ከ10:00 ጀምሮ ሲካሄድ ያመሸ ሲሆን “ብሔራዊ ክብር፣ በሕብር” በሚል መሪ መፈክር ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ዜጎች በእንግሊዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ለውጭ አገራት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዛሬው የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሚቃወመው ዘመቻ
“ግድቡ የእኔ ነው፣ ግድቡ ገንዘቤ-አባይ ደግሞ ወንዜ ነው፣ አባይ ሀብታችን ስለሆነ እንገድበዋለን፣ መምረጥ መብታችን ስለሆነ እንመርጣለን፣ ሰላማችን ጌጣችን ስለሆነ ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን” የሚሉ ግልፅ መልፅክቶች ሲተላለፉ አምሽተዋል።

በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በይፋ በተጀመረው መርሃ ግብር ላይ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን አስተባባሪዎቹም “ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩንም ልዩነቶቻችን ከሀገራችን በታች መሆናቸውን ስለምንረዳ እና በሉዓላዊነታችን ስለማንደራደር ሀገራችን ላይ ለሚቃጡ ማናቸውም የውጭ ተፅዕኖዎች በአንድነት እንቆማለን” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል፣ መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚካሄደውን የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ደብዳቤ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መላኩን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ወይም አንድ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት በውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሞክሩትን ኹሉም የውጭ ኃይሎችን እንደሚያወግዝ በደብዳቤው ያመለከተው
ምክር ቤቱ፣ ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የዴሞክራሲ ምሰሶዎች አንዱ የሆነውን ግልጽ ምርጫ ለማካሄድ ገለልተኛ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሟንና ይህም ለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሽግግር አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስም “የምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ወይም አንድ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት በውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሞክሩ ኹሉንም የውጭ ኃይሎችን አጥብቀን እናወግዛለን” ብሏል።

“የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ ጉዳዮች የሰጠውን ትኩረት እያደነቅን በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ጣልቃ ገብነት ግን የሚያስከተለው አደጋ ያሳስበናል” ያለው ይኸው ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ እንደሆነና የትኛውም ሉዓላዊ ሀገር እንዲህ አይነት ክህደት ሲፈጸምበት ሊወስደው የሚችለውን እርምጃ የኢትዮጵያ መንግሥት መውሰዱን አስታውሶ “የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ሊደገፍ ይገባል” ብሏል።

“ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከኢትዮጵያ ጋር የምትሠራው አሜሪካ ኢትዮጵያንና ቀጣናውን ለማተራመስ የሚሠራውን የሕወሓት የሽብር ቡድን ደጋፊዎችና የውጭ ተባባሪ ድርጅቶችን መከታተል ይኖርባታል። አሜሪካ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ፣ ለሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ድጋፍ እንደምትሰጥና በኢትዮ-ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ እንዲሁም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የሚካሄደው የመልሶ ግንባታና የሰብዓዊ ድጋፍን በማገዝ አሜሪካ ገንቢ ሚና እንደምትጫወት እምነታችን ነው። ከ115 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውና በፕሬዚዳንት ቴዲ ሩዝቬልት የመሪነት ዘመን የተጀመረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ጠንካራ ወዳጅነት እና የረጅም ጊዜ አጋርነት በጋራ ብልጽግና ወደፊት እንደሚራመድም እናምናለን” ሲል
ሲልም ምክር ቤቱ በደብዳቤው አመልክቷል።

LEAVE A REPLY