የአማራ ባህል ማዕከል በአዲስ አበባ ለመገንባት 42,200 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጠ!

የአማራ ባህል ማዕከል በአዲስ አበባ ለመገንባት 42,200 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጠ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየአማራ ባህል ማዕከልን በአዲስ አበባ የመገንባት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ትናንት በአንድነት ፓርክ የተካሄደ ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአዲስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ለአማራ ባህል ማዕከል መገንቢያ የሚሆን 42ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስረክበዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ በርካታ እንግዶች በተገኙበት በዚሁ መድረክ እንደተገለፀው፣ የአማራ ልማት ማህበር/አልማ የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ለባህል ማዕከል ግንባታው ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡ ታውቋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለባሕል ማእከሉ መገንቢያ የሚሆን ቦታ በመስጠቱ በክልሉ ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበው፣ የባሕል ማእከሉ የአማራ ሕዝቦች ቱባ ባሕል እና ትውፊት የሚታይበት፣ የማንነታቸው መገለጫ ሆኖ እንዲገነባ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤት አስታውቋል።

የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ በከተማ አስተዳደሩ በመገንባት ላይ ያሉትን የማዘጋጃ ቤት እድሳት፣ የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት፣ የታላቁ ቤተ መፃሕፍት፣ የመስቀል አደባባይ እና የቤተ መንግስት የመኪና ፓርኪንግ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሂደት የጎበኙበት መርኃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

በዚሁ የጉብኝት መርኃ ግብር ላይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሽመልስ እሸቱ፣ ለሚዲያ ባለሙያዎቹ በሰጡት ማብራሪያ፣ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ (ማዘጋጃ ቤት) ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በዘመናዊ እና ለስራ ምቹ በሆነ መልኩ እየታደሰ መሆኑን፣ በህንፃው ውስጥ የሚገኘው ባህልና ቴአትር አዳራሽን ጨምሮ አጠቃላይ የህንፃው እድሳት ክንውን ከ71 በመቶ መጠናቀቁ ታወቋል።

4.6 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተከናወነ ያለው የአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክትም የአድዋን ታሪክ ለመዘከር በሚያስችል መልኩ እየተሰራና በውስጡ የአድዋ ሙዚየም፣ ዘመናዊ ላይቤሪያ እና የታሪክ ልህቀት ማዕከል እንደተካተቱበት፣ የፕሮጀክቱ አፈጻጸምም ከ60 በመቶ በላይ መድረሱንና በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ወራት አካባቢ ላይ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተመልክቷል።

1.1 ቢሊዮን ብር የተበጀተለትና 19ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የታላቁ ቤተ መጽሃፍት ግንባታም 93 በመቶ መድረሱን፣ ሲጠናቀቅም ከ5 ሺህ እስከ 7 ሺህ የዲጂታል ላይብረሪ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተናግረዋል።

በዛሬው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት ጉብኝት መርኃ ግብር ላይ፣ በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የታላቁ ቤተ መንግስት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ፓርኪንግ ፕሮጀክትም አጠቃላይ የግንባታ ክንውኑ 79 በመቶ መድረሱንና ለ1 ሺህ ተሽከርካሪዎች የፓርኪንግ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም ኢንጅነር ሽመልስ ገልፀዋል።

የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለልዩ ልዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሆኖ መሰራቱን፣ እንዲሁም በአንድ ጊዜ 1ሺህ 400 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ ፓርኪንግና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት በሚያስችል መልኩ ግንባታው ተጠናቆ በቅርብ ቀን አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አስታውቀዋል፡፡

LEAVE A REPLY