ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የትግራዩ ጦርነት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያቀረብኩት ሀሳብ ተቀባይነት አላገኘም” በሚል፣ አሜሪካ በኢትዮጵያና ኤርትራ ባለስልጣናት፣ ወታደራዊና የደህንነት ሹማምንት፣ በአማራ ክልል አስተዳደርና የፀጥታ መዋቅር መሪዎች ላይ ማእቀብ ጥላለች።
“በወንጀል የተሳተፉ” ባለቻቸው የሕወሓት አመራሮች ላይ የጉዞ ማዕቀብ በመጣል፣ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን የኢኮኖሚ ማበረታቻ እና የፀጥታ ድጋፍም ማቋረጧን አስታውቃለች።
አሜሪካ ይፋ ባደረገችው የጉዞና የኢኮኖሚ ማዕቀብ መግለጫ፣ የጉዞ ማዕቀቡ በየትኞቹ ባለስልጣናት ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን በስም ጠቅሳ የሰጠችው መረጃ የለም፤ ይሁንና የኢኮኖሚ ማዕቀቡ ለሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ለትምህርት፣ ግብርናና ጤና ለመሳሰሉት ታደርግ የነበረውን የልማት ዕርዳታ የማያካትትና ልገሳዋን የምትቀጥል መሆኑን በግልፅ አስቀምጧል።
ከማዕቀቡ ባሻገር፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ግድያና መሰል ወንጀሎች የተሳተፉ ወገኖችን፤ ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ ለፍርድ እንዲያቀርቡ የሚጠይቀው የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ደንብ ቁጥር /Section 212A የተሰኘውን የሀገሪቱ የህግ ማዕቀፍን መሰረት አድርጎ የተላለፈ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ በዚህ ደንብ መሰረት የሚተላለፍ የጉዞ እገዳ ውሳኔ ዒላማ ያደረጋቸውን ሰዎች ማንነት በስም አለመጥቀስን እንደሚፈቅድም ተመልክቷል።
ይሁንና፣ አሜሪካ ከዚህ ቀደም የከፋ የሰብዓዊ መብት ረገጣና የሙስና ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ስራ ላይ የምታውለው የማዕቀብ አይነት (ደምብ ቁጥር/Section) 7031C የተሰኘውን እንደነበርና በዚህ ደንብ መሰረት የሚሰጥ የማዕቀብ ውሳኔም ዒላማ ያደረጋቸውን ባለስልጣናትና ግለሰቦች ስም ዝርዝር በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት በኩል ለህዝብ ይፋ መሆንን የሚያዝ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ም/ቤት በትግራይ ጦርነት የሚሳተፉ ወገኖች ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲደረግ የሚጠይቀውን ውሳኔ ስም ማሳወቅን በማያስገድደው ውሳኔ ደንብ ቁጥር /Section 212A በኩል ተፈፃሚ እንዲሆን ማስደረጉ “ለምን?” የሚል ግራ መጋባት እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል።
በተያያዘ፣ የአሜሪካ የቪዛ ክልከላ ውሳኔ “የኢትዮ-አሜሪካን ረጅም እና ወሳኝ የሁለትዮሽ ግንኙነት የማይመጥንና አግባብነት የሌለው ነው” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።
ውሳኔው የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ አስተዳደር ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ በአዎንታዊ እና ገንቢ በሆነ መልኩ እየሠራ ባለበት ወቅት የተላለፈ መሆኑን የጠቀሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና ለመፍጠር የተላለፈው የቪዛ ክልከላ አግባብነት የሌለውና አሳዛኝ መሆኑን አስታውቋል።
“በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ በተቃረበበት ወቅት የተወሰነ የተሳሳተ ውሳኔ ነው” ያለው ሚኒስቴሩ “በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እንጂ አላስፈላጊ የሆነ ውሳኔን አይጠብቅምም። የቪዛ ክልከላ ውሳኔው የኢትዮ -አሜሪካን ረጅም እና ወሳኝ የሁለትዮሽ ግንኙነት የማይመጥንና የሀገራቱን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ሊጎዳው የሚችል ነው” ብሏል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርገው ሙከራ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር እርምጃው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በሚል የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው፣ መቀመጫውን ኬኒያ ናይሮቢ ያደረገው የቴሌግራፍ መጽሔት የአፍሪካ ወኪል ዘጋቢ ዊል ብራውን፣ “ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር እርምጃው የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች” ሲል ያቀረበው መረጃ ስህተት መሆኑን ገልጿል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት በሰጠው በዚሁ መግለጫ “መጽሔቱ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል በተካሄደው ሕግ የማስከበር እርምጃ የኬሚካል ጦር መሳሪያ በመጠቀሙ ንጹሐን ላይ ጉዳት ደርሷል ሲል ሐሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል” በማለት ውንጀላው መሰረተ ቢስ እና ሐሰተኛ መሆኑን አመላክቷል፡፡
“ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ስምምነት የተከለከለውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ በሕዝቦቿ ላይ አትጠቀምም፤ አልተጠቀመችምም” ያለው መግለጫው፣ ኢትዮጵያ ለፍትሕ እና ለሕግ ተገዥ በመሆኗ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተከለከለውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ በሕግ ማስከበር እርምጃው የምትጠቀምበት ምንም አይነት ምክንያት አለመኖሩንም አስታውቋል፡፡
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የተሳሳተ እይታ እንዲኖር መሰል ኃላፊነት የጎደላቸው እና የተሳሳቱ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆናቸውን ቀድሞ እንደገለፀ ያሳወቀው ይኸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ውጥረቶችን ለማባባስ ያለመ ነው። ይህም በተለያዩ አካላት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል አንዱ ነው” ብሏል፡፡