በሊቢያ በረሃ መከራዎችን ያሳለፈችው ኢትዮጵያዊት “ከንጋት ጀርባ” የተሰኘ መጽሐፍ አሳተመች!

በሊቢያ በረሃ መከራዎችን ያሳለፈችው ኢትዮጵያዊት “ከንጋት ጀርባ” የተሰኘ መጽሐፍ አሳተመች!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– 250 ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያንና ሶማሊያዊያን ካለቁበት የሜዲትራኒያን ባህር የጀልባ መስጠም አደጋ፣ ደላላው ረስቷት በመቅረቷ በተአም የተረፈችው ኢትዮጵያዊቷ ኤልሳቤት አለበል፣ መፅሐፍ አሳተመች።

400 ስደተኛ ወገኖቻችንን ኢንተርቪው አድርጋ፣ ስደተኛ ወገኖቻችን ስለሚደርስባቸው ሰቆቃና ግፍ የሚያወሳና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ “ከንጋት ጀርባ” የተሰኘ ባለ406 ገጽ መጽሀፍ አሳትማ ለገበያ ማቅረቧን ኤልሳቤት ዛሬ አስታውቃለች።

በአሁኑ ወቅት ቋሚ መኖሪያዋን በሰሜን አሜሪካ ያደረገችውና በዚያው አገር የፊልም ትምህርቷን ተከታትላ በተዋናይነት እና በካስቲንግ ዳይሬክተርነት እየሰራች የምትገኘው ኤልሳቤት አለበል፣ ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ “ከንጋት ጀርባ” የተሰኘው መጽሐፏ ከእዚህ ቀደም Behind the sunrise በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ በአሜሪካን ለንባብ መብቃቱን ተናግራለች።

ይህ መጽሀፍ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 23/2013 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር በሚከናወን ደማቅ ስነ ስርዓት የሚመረቅ መሆኑን የገለፀችው ደራሲዋ፣ በፕሮግራሙ ላይ በታዋቂ የስነ ጽሁፍ ባለሙያዎች የመጽሐፉ ዳሰሳ፣ በሙዐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረትና ዶክተር ወዳጄነህ መሐረነ ዲስኩር፣
ከመጽሐፉ የተመረጡ ንባቦችን አርቲስት አለማየሁ ታደሰና አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ፣ በእፀገነት ከበደ ወግ፣ በበላይ በቀለ ወያ ግጥሞች እንደሚቀርቡ አመልክታ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፕሮግራሙን በነፃ እንዲታደም ጋብዛለች።

LEAVE A REPLY