ባይደን ብሔራዊ ዕርቅ እንዲደረግ ጠይቁ! ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ከሽብርተኛው ሕውሓት ጋር መደራደር ተቀባይነት...

ባይደን ብሔራዊ ዕርቅ እንዲደረግ ጠይቁ! ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ከሽብርተኛው ሕውሓት ጋር መደራደር ተቀባይነት የለውም አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅና ሀገሪቱን ወደመረጋጋት ለመመለስ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ትናንት ማምሻውን ከዋይት ሐውስ የወጣው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መግለጫ አስታውቋል።

በትግራይ የሚደረገው ጦርነት ያስከተለው ስብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን ያወሱት ባይደን እየተፋለሙ ያሉ ወገኖች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ፣ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ኋይሎች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በትግራይ ያለው የስብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ከ40 አመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የረሀብ አደጋ በማንዣበቡ ሁሉም ተፋላሚ ሀይላት የሰላም መንገድ እንዲከተሉ እና ዕርዳታ ያለምንም መስተጓጎል ለተቸገሩት እንዲደርስ መንግስት ሀላፊነቱን እንዲወጣ የጠየቁት ባይደን፣ አሜሪካ ከአፍሪካ ህብረትና ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት አስታውቀዋል።

“የኢትዮጵያ መንግስትና ተቋማት፣ ለብሄራዊ እርቅና መግባባት ቅድሚያ ሰጥተው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን በማቆም ወደ ውይይትና የጋራ ሀገራዊ መግባባት መድረስ አስፈላጊ ነው” ሲሉም ባይደን አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በዚሁ መግለጫቸው፣ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፊልትማን በዚህ ሳምንት ወደ ቀጠናው እንደሚመጡ ገልፀው “አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሁሉንም ሀገሮች ፍላጎት ያማከለ ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት አላት” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ትናንት በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የጉዞ እገዳ ማዕቀቦች በግልጽ የተቃወሙት ታዋቂው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ፣ በአሜሪካ የእንደራሴዎች ምክር ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያላቸውን ሀሳብ አቅርበዋል።

“የኢትዮጵያ መንግስትን ከሽብርተኛው ድርጅት ሕውሓት ጋር በተመሳሳይ ረድፍ ለማስቀመጥ መሞከር ተቀባይነት የለውም” ሲሉ በሴኔቱ ፊት የተናገሩት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ “የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማምጣት እየሰራ ይገኛል፤ ሰላምንና አንድነትን ከማምጣት ውጪ ሌላ አካሄድ አልሄደም” ብለዋል።

“ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንደተነገረው በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ተግባር ነው። በዚህ ሁኔታ በአገሪቱ ሰላምን ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን መንግስት ከሽብር ድርጅቱ ህወሓት ጋር በእኩል ማስቀመጥ ተቀባይነት የሌለው ነው። በዋናነት መታወቅ ያለበት ጉዳይ ህወሓት የሽብር ድርጅት መሆኑ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ለ19 ጊዜያት ያህል መጎብኘታቸውንና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግስት በአገሪቱ አንድነትንና ሰላምን ለማምጣት እየሰራ መሆኑን መነጋገራቸውን ያመለከቱት ሴናተሩ፣ በተለይም የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት ዳግም በመመለሳቸው የአለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን አስታውሰው፤ መንግስት ለቀጠናው ሰላምና ደህነንነት እያከናወነ ያለውን ተግባርም ለሴኔቱ አስገንዝበዋል።

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአዲስ መልክ ካቢኔያቸውን አቋቁመው በሁሉም አካባቢ ወደ ስራ በሚገቡበት ወቅትም ሽብርተኛው ድርጅት ደስተኛ አልነበረም። እናም ይህ የህወሓት የሽብር ቡድን ከማእከላዊ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት በማቋረጥ ወደ ግጭት መግባት ጀመረ” በማለት በአሜሪካ የእንደራሴዎች ምክር ቤት ፊት የተናገሩት ጂም ኢንሆፍ፣ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በአገሪቱ መከላከያ ጦር ላይ ጥቃት መፈጸሙንና መንግስትም ይህንን ተከትሎ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ መግባቱን አውስተው፣ በዚህ ወቅት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ጥፋቶችን ለመመርመርና ተጠያቂነትን ለማምጣት የኢትዮጵያ መንግስት ከተመድ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንና ይህም እየተተገበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

“የአሜሪካ መንግስትም ይህንን ሂደት በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም ይገባል። ለኢትዮጵያውያን እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‘እየሰራችሁ ያላችሁትን ስራ እንደግፋለን አብረናችሁ ነን ለማለት እወዳለሁም’ ሲሉም የሪፐብሊካን ፓርቲ አባሉና የኦክላሆማ ሴናተሩ ጂም ኢንሆፍ አጋርነታቸውን ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY