ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ከአንድ ታካሚ ሆድ ውስጥ በርካታ የተለያዩ የስለት መሳሪያዎች በቀዶ ጥገና ህክምና ሊወጡ እንደቻሉ የገለፁት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ተሾመ፣ በታካሚው ሆድ ውስጥ የነበሩ በርካታ ሚስማሮች፤ እስክሪቢቶዎችና ሌሎች የስለት ቁሳቁሶች በቀዶ ሕክምና መውጣታቸውን አስታውቀዋል።
ሕመምተኛው ታራሚ እና የአዕምሮ በሽተኛ እንደሆነና ከዕለታት አንድ ቀን እስክሪቢቶ ሲውጥ ያየ ሌላ ግለሰብ በሰጠው መረጃ መሠረት ህክምናውን ለማድረግ መገደዳቸውን የገለፁት ስራ አስኪያጁ፣ የሆስፒታሉ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ባደረጉት ክትትል እና በጨረር ምርመራ፣ እስክሪቢቶን ጨምሮ
የተለያዩ ስለት ያላቸው ቁሳቁሶች ሆዱ ውስጥ መታየታቸውና
ግለሰቡ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር በጋሻው መለሰ በበኩላቸው፣ ታካሚው መርፌንና ሌሎች ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በ4 ወራት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት መዋጡን፣ እንዲሁም ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የስነ ልቦና ክትትልም እየተደረገ በመሆኑ መሻሻል እየታየበት መሆኑን ገልጸው፣ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን ልዩ ባህሪያትና ጤናቸውን በንቃት መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።