ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የምስክርነት ጥበቃቸው ተነስቶ ትናንት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በድጋሚ መቅረባቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ወይዘሮ ኬሪያ ከተከሳሽነት ወደ ምስክርነት ተቀይረው መቆየታቸውንና ተጠርጣሪዋ በጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በገቡት ሥምምነት መሠረትም በገዛ ፈቃዳቸው በጽሑፍና በሲዲ ዝርዝር የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተው እንደነበር ያስታወሱት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን፣
በፍርድ ቤት ውሳኔ ከእስር እንደተለቀቁና ጎን ለጎንም ለግለሰባቸው አስፈላጊው የምስክርነት ጥበቃ ሲደረግ መቆየቱንም አመልክተዋል።
“ይሁንና ወይዘሮ ኬሪያ ቆይተው ምስክር የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው፣ እንዲሁም ምስክርነት ሲሰጡ የቆዩት ተገደው እንደነበር በመግለጻቸው ምስክርነታቸው ሊቋረጥ ችሏል” ያሉት
አቶ አወል ሱልጣን፣ በምስክሮችና ጠቋሚዎች አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 11 መሰረት፣ የጥበቃ ተጠቃሚው ስምምነቱንና ግዴታውን የማያከብር ከሆነ፣ የጥበቃ ስምምነት ውሉ ስለሚቋረጥ አቃቤ ሕግም ለወይዘሮ ኬሪያ ምስክር በመሆናቸው ይሰጣቸው የነበረውን ጥበቃ ለማንሳት መገደዱን አስረድተዋል።
አቶ አወል ሱልጣን አያይዘውም “ከዚህም በኋላ ወይዘሮ ኬሪያ ከዚህ ቀደም በተጠረጠሩበት ወንጀል የቅድመ ምርመራ ስራ እንዲጀመር አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል” በማለት፣ የተጠርጣሪዋ ጠበቆች “በጉዳዩ ላይ ለመከራከር አልተዘጋጀንም” በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ወይዘሮ ኬሪያ በመጪው ሰኞ ዳግም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማዘዙንና እስከ መጪው ሰኞም በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ገልፀዋል።