ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሮበርት ጎዴክ፣ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት ተሳታፊዎች አካሔዳቸውን ካልቀየሩ አገራቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል አስጠነቀቁ።
ኃላፊው፣ በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ፊት ትናንት ቀርበው፣ በኢትዮጵያ ቀውስ ላይ አገራቸው እየተከተለች ያለችውን የምላሽ አሰጣጥ ያስረዱ ሲሆን፣ የፀጥታው ሁኔታ ከቀናት ወዲህ ተባብሶ መቀጠሉም የሰብዓዊ ቀውሱን አደገኛ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው አመልክተዋል።
“የአሜሪካ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትንተና፣ የቀጠለው ግጭት ወደ ጠኔ የሚጠጋ ሁኔታ መፍጠሩን ያሳያል። በተመጣጠነ ምግብ እጦት እና በረሀብ ሰዎች ለመሞታቸው የተረጋገጠ መረጃ አለ” ያሉት ኃላፊው፣ በትግራይ ክልል ያለው ግጭትና የሰብዓዊ ቀውስ እንዲሻሻል በቁርጠኝነት የማይሰሩ ከሆነ አገራቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ልትወስድ እንደምትገደድ አስጠንቅቀዋል።
በውጊያው፣ በፍተሻ ኬላዎች ህገወጥ ተግባር፣ በሥርዓተ አልበኝነት እና በተዋጊ ኃይሎች ወከባ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች እንቅስቃሴ ችግር እንደገጠመው የተናገሩት ሮበርት ጎዴክ፣ ለዚህም የዩስኤይድ አጋር ባልደረባ እና ሌሎች ሰባት የእርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች መገደላቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።
“ሙሉ የተኩስ አቁም፣ ሙሉ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እንቅስቃሴ፣ የሰላማዊ ሰዎች ደህንነት ጥበቃ እንፈልጋለን። የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ክልል ኃይሎች ለቀው ሊወጡ ይገባል። ቀውሱ በፖለቲካዊ መንገድ መፍትሔ እንዲበጅለትም በትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ በደሎች እና የጭካኔ ድርጊቶች ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራ ሊደረግ እና ፈጻሚዎች ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል።