ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ነዋሪነቷን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት አድርጋ ሙዚቃን እዚያው የተማረችው ድምፃዊት ሳምራዊት አሰፋ፣ አዲስ ያወጣችው የሙዚቃ አልበሟ ሽያጭ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ለሚደርስባቸው ሴቶችና ህጻናት መርጃ እንደሚውል ገልፃለች።
ከአሁን ቀደም ነጠላ ዜማዎችን የለቀቀችውና በካሊፎርኒያ ግዛት የሙዚቃ መምህርት ሆና በመስራት ላይ ያለችው ሳምራዊት አሰፋ፣ ለአዲሱ የሙዚቃ አልበሟ “ሴት” የሚል መጠሪያ የሰጠችው ሲሆን፣ ይህንን ያደረገችውም ለሴት ልጅ ያላትን ክብርና አድናቆት ለመግለጽ እንደሆነ ተናግራለች።
አዲሱን አልበሟን ወደኢትዮጵያ ተመልሳ የማስመረቅና ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመድረክ የመጫወት ፍላጎት እንደነበራት የገለፀችው ድምፃዊቷ፣ ይሁንና ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ፍላጎቷን እንደገደበው አመልክታ፣ ይህን ማድረግ ባትችልም ግንጨበቅርቡ በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አማካኝነት ሁሉም ሰው ባለበት ሆኖ የሚታደምበት የሙዚቃ ድግስ ለማዘጋጀት እየተሰናዳች መሆኗን አስታውቃለች።