ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፣ ኮሚሽኑ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የምርጫ ተሳታፊዎች ጋር እያካሄደ በሚገኘው ውይይት ላይ፣ በምርጫው ወቅት ተግባራዊ መደረግ አለበት የተባሉትን ባለስድስት ነጥብ አጀንዳዎች ይፋ አድርገዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች ከሰብአዊ መብቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እና የሚወስዷችውን እርምጃዎች በተመለከተ በምርጫ መወዳደሪያ ጥሪ ሰነዳቸው (ማኒፌስቷቸው) ውስጥ እንዲያካትቱ የሚጠይቀው ባለስድስት ነጥብ አጀንዳው፣ ፓርቲዎች በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደማይታገሱ በይፋ ማሳወቅ እና ምርጫው ለስርዓተ ፆታ ምላሽ ሰጪ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው፣ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት የሆኑ ህጎችን ፖሊሲዎችን እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለመፈተሽ እና ለማሻሻል በይፋ ቃል እንዲገቡ፣ የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀት፣ መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነጻነት መግለጽ መብት በሁሉም ተሳታፊ አካላት፣ በመንግስት ኃይሎች እና በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስታውቆ “ከግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ መቆጠብ ይገባል” ሲልም በስድስተኛው ነጥብ አስገንዝቧል።
በውይይቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ኮሚሽኑ ያወጣቸውን ባለስድስት ነጥብ አጀንዳዎች እንደሚደግፍ እና ለተፈጻሚነታቸውም እንደሚሰራ አስታውቋል።