ኢትዮጵያ ነገ ዜና:- በመላው ዓለም እጅግ ዝነኛ ከሆነው የአሜሪካው Meharshi university ጋር በመተባበር በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትምህርት በመስጠት ላይ የሚገኘው አሜሪካ ኮሌጅ ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ በኮምፒዩተር ሳይንስና በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የትምህርት ዘርፎች በማስተርስ ፕሮግራም ያስተማራቸውን ተማሪዎች ትናንት እሁድ ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በደማቅ ስነ ስርዓት በካፒታል ሆቴል ባስመረቀበት ወቅት፣ አቤል አረጋዊ የተባለ ተመራቂ ተማሪ 4 ነጥብ በማምጣት የማዕረግ ተመራቂ ለሆችው ርብቃ እሸቱ በመድረኩ ላይ ተንበርክኮ “የታገቢኛለሽ ወይ” ጥያቄ አቅርቦላታል።
የላቀ ነጥብ አምጥተው በማዕረግ ከተመረቁ ወንድ ተማሪዎች አንዱ የሆነው አቤል አረጋዊ፣ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ “ታገቢኛለሽ ወይ” የሚለውን ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት ባደረገው አጭር ንግግር፣ እርሱና የፍቅር አጋሩ በኮሌጁ የተማሪነት ዘመናቸው ያሳለፉትን ደስ የሚል ጊዜ አውስቶ “የእሷ በትምህርቷ ጎበዝ መሆን እኔንም አጎብዞኛል።
አብረን በምንሆንባቸው ጊዜያትም በጥናታችን እንድንተጋ በማድረጓና ያልገባኝንም እያስረዳችና እያስጠናችኝ ተያይዘን ለዛሬው ትልቅ ውጤት እንድንደርስ አስችላለች። ከእርሷ ጋር በቆየሁበት የሁለት አመታት ጊዜ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አግኝቻለሁ። ከእርሷ ጋር ተጋብተን ብንኖር ደግሞ የበለጠ ውጤታማና ስኬታማ እንደምንሆን ስላመንኩም ዛሬ በእናንተ ፊት ይህን ላደርግ ወድጃለሁ” ብሏል።
ከዚህ ንግግሩ በማስከተልም፣ ተንበርክኮ የእጮኛነት ማሰሪያ የሆነውን የቃል ኪዳን ቀለበት በጣቶቿ አጥልቆላታል። እጮኛው ርብቃ በበኩሏ፣ ለአቤል የጋብቻ ጥያቄ በእንባ ታጅባ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥታለች። ይህም ለምረቃ ስነ ስርዓቱ የተለየ ድምቀት ሰጥቶታል።
አሜሪካ ኮሌጅ ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ በማስተርስ ፕሮግራም ያስተማራቸውን ተማሪዎቹን ባስመረቀበት በዚሁ ፕሮግራም ላይ፣ የኮሌጁ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር አስማማው አጥናፍ፣ በየትኛውም የአለም ክፍል የሚኖር ሰው የኢትዮጵያን ዲግሪ መማር የሚችልበትና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተግባር ላይ የዋለ የኦንላይን ትምህርት በኮሌጁ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።