ም/ከንቲባዋ በአዲስ አበባ 500 ሺህ ቤቶች ለማስገንባት የሚያስችል የመግባብያ ሰነድ መፈረሙን አስታወቁ!

ም/ከንቲባዋ በአዲስ አበባ 500 ሺህ ቤቶች ለማስገንባት የሚያስችል የመግባብያ ሰነድ መፈረሙን አስታወቁ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  “የከተማ አስተዳደሩ በርካታ የቤት አቅርቦት አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን ቤቶች በላይ ለመገንባት እየሰራን እንደሆነ ይታወቃል።

ባሳለፍነው ግንቦት 12/ 2013 ዓ.ም 30 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በውጭ ባለሃብቶች ለማስገንባት የሚያስችል የመግባብያ ስምምነት ሰነድ መፈረማችንም ይታወሳል” በማለት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ያመለከቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ “ዛሬም የከተማ አስተዳደሩ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው ፕሮጀክት 2000 የሪል እስቴት አልሚ ኩባንያ ጋር፣ 500 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል” ሲሉ አስታውቀዋል።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ ባስተላለፉት በዚሁ መልዕክታቸው “ይህ ስምምነት በመጀመሪያው ዙር 100 ሺህ ቤቶች የሚያስገነባ ሲሆን፣ በመጪዎቹ አምስት አመታት ጊዜ ውስጥ 500 ሺህ ቤቶች ተገንብተው የሚጠናቀቁ ይሆናል። ለግንባታው ወጪ የሚሆነውን 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አልሚ ኩባንያው የሚሸፍን እና በ30 አመት ውስጥ የሚከፈል 1 ፐርሰንት ወለድ የሚኖረው ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ለግንባታ የሚያስፈልገውን መሬት እና ግብዓቶች ለማቅረብ ዝግጁ ይሆናል” ያሉት ምክትል ከንቲባዋ “ይህ ፕሮጀክት የነዋሪያችንን የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ከማመጣጠን ባለፈ ለከተማችን ብሎም ለአገራችን ወጣቶች ፣ የኮንስትራክሽን ተመራቂዎች ፣ ሴቶች ፣ ስራ ፈላጊዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል” ብለዋልተ

በመልዕክታቸው ማጠቃለያም “በቤት እጦት ለምትንገላቱ የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉ እንኳን ደስ አለን እያልኩ፣ አዲስ አበባን ለነዋሪዎችዋ ምቹ ቤት እና ለኑሮ ተስማሚ እንድትሆን የጀመርነውን ስራ እና የገባነውን ቃል አክብረን እንተገብራለን” በማለት ምክትል ከንቲባዋ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ቃል ገብተዋል።

LEAVE A REPLY